በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ታትያና ዛጉሊና ከባለቤቷ ከዲሚትሪ ጋር

መጋቢት 17, 2021
ሩሲያ

በቢሮቢድዣን እህት ታትያና ዛጉሊና ሊፈረድባት ይችላል

በቢሮቢድዣን እህት ታትያና ዛጉሊና ሊፈረድባት ይችላል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኟን ውድቅ አደረገ

መስከረም 16, 2021 የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል ፍርድ ቤት እህት ታትያና ዛጉሊና ያቀረበችውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። መጀመሪያ ላይ የተላለፈባት ፍርድ በዚያው ይጸናል። በአሁኑ ወቅት ወህኒ አትወርድም።

መጋቢት 31, 2021 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት እህት ታትያና ዛጉሊና ጥፋተኛ ናት የሚል ፍርድ ያስተላለፈ ሲሆን የሁለት ዓመት ከስድስት ወር የገደብ እስር በይኖባታል።

አጭር መግለጫ

ታትያና ዛጉሊና

  • የትውልድ ዘመን፦ 1984 (ሴልዬክትሲኦንናያ መንደር፣ ትራንስ ባይካል ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ የፋሽን ዲዛን ተምራለች። ጥፍር የማሳመር ሥራ እንዲሁም ልብስ ስፌት (በዋነኝነት የሠርግ ቀሚሶችን ማስተካከል) ትሠራ ነበር። መረብ ኳስ፣ የጠረጴዛ ቴኒስ፣ ዳንስ እና ሹራብ ሥራ ትወዳለች

    ከልጅነቷ ጀምሮ ተፈጥሮን ትወዳለች፤ በፈጣሪም ታምናለች። ከጊዜ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። በ2010 ተጠመቀች። በ2012 ከዲሚትሪ ጋር ትዳር መሠረተች

የክሱ ሂደት

ግንቦት 17, 2018 150 የሕግ ባለሥልጣናት የ22 የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶችን ፈተሹ። ባለሥልጣናቱ ይህን ዘመቻ “የፍርድ ቀን” የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የአካባቢው የምርመራ ቢሮ በክልሉ በሚገኙ 22 ወንድሞችና እህቶች ላይ የወንጀል ክስ መሥርቷል። የካቲት 6, 2020 ታትያናን ጨምሮ በስድስት እህቶቻችን ላይ በጽንፈኝነት እንቅስቃሴ ተካፍለዋል በሚል ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

ታትያና ፍርድ ቤት የቀረበችው መስከረም 17, 2020 ነው። የሚተላለፍባትን ብይን እየተጠባበቀች ባለችበት በዚህ ጊዜ ባለሥልጣናቱ ከክልሉ ውጭ እንዳትጓዝ የከለከሏት ከመሆኑም ሌላ የባንክ ሒሳቦቿን አግደውባታል።

ታትያና ሁኔታውን ለመቋቋም እንዲሁም መስበኳን እና ለእምነቷ ጥብቅና መቆሟን ለመቀጠል የረዳት ጸሎት እና ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ እንደሆነ ገልጻለች። እንዲህ ብላለች፦ “ባለሥልጣናቱ መጥተው በሬን በኃይል ሲያንኳኩት ተደናግጬ ነበር፤ ሆኖም ወዲያውኑ ጸለይኩ። ከዚያ በኋላ መረጋጋት ቻልኩ።”

ለምሳሌ፣ ቤቷ በተፈተሸበት ወቅት ከፖሊሶቹ ለአንዱ በዚያ ዕለት እምነቷ ይበልጥ እንደተጠናከረ ነገረችው። ይህን ያለችው ለምን እንደሆነ ሲጠይቃት ታቲያና፣ ኢየሱስ በዮሐንስ 15:20 ላይ የተናገረው ሐሳብ በእሷ ላይ እየተፈጸመ እንዳለ ገለጸችለት። ኢየሱስ “ባሪያ ከጌታው አይበልጥም . . . እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል” ብሎ ነበር። ታትያና እንዲህ ብላለች፦ “አንደኛው ፖሊስ ‘የምትናገሪው ነገር እኮ ኢየሱስን ከሰቀሉት ሰዎች አንዱ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አደረገኝ’ አለ። በዚያ ወቅት እምነቴ የተጠናከረ ከመሆኑም በላይ ውስጣዊ ሰላምና ደስታ ተሰማኝ። ይሖዋ ከጎኔ ሆኖ እየደገፈኝ እንደሆነ ተሰማኝ!” ታትያና መጀመሪያ ላይ ፍርድ ቤት ስትቀርብ ፈርታ ነበር። ይሁንና ይሖዋ ድፍረት እንዲሰጣት ከጸለየች በኋላ “አሁን የምናገረው በልበ ሙሉነት ነው” ብላለች።

ይሖዋ በሩሲያ የሚኖሩ ውድ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን እየደገፋቸው እንዲሁም ‘የእምነት ሥራቸውን፣ ከፍቅር የመነጨ ድካማቸውንና ጽናታቸውን’ እየባረከ በመሆኑ እናመሰግነዋለን።—1 ተሰሎንቄ 1:2, 3