የካቲት 18, 2020
ሩሲያ
በቺታ፣ ሩሲያ የሚገኙ ፖሊሶች በወንድም ቫዲም ኩትሰንኮ ላይ ከፍተኛ ሥቃይ አድርሰውበታል
የካቲት 10, 2020 ምሽት ላይ በቺታ፣ ሩስያ የሚገኙ ፖሊሶች የይሖዋ ምሥክር በሆነው በወንድም ቫዲም ኩትሰንኮ ላይ ከፍተኛ ሥቃይ አድርሰውበታል። ፖሊሶቹ ወንድማችንን በተደጋጋሚ የደበደቡትና ያነቁት ሲሆን ሆዱንና እግሩን በኤሌክትሪክ በመንዘር አሠቃይተውታል። ፖሊሶቹ ወንድም ኩትሰንኮን ያሠቃዩት ስለ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች መረጃ እንዲሰጣቸው ለማስገደድ ነበር።
በዚያ ቀን ማለዳ፣ የፌዴራል ደህንነት አገልግሎት ፖሊሶች የወንድም ኩትሰንኮን ጨምሮ በቺታ የሚገኙ 40 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈትሸዋል። ከሌሊቱ 5:00 ላይ የሩሲያ ልዩ ኃይሎች ወንድም ኩትሰንኮን ከሚስቱ እናት ቤት ወሰዱት። ፖሊሶቹ ወንድም ኩትሰንኮን በካቴና አስረውና ፊቱን ሸፍነው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ጫካ በመውሰድ አሠቃይተውታል። ወንድም ኩትሰንኮ ከፍተኛ ሥቃይ የደረሰበት ቢሆንም ስለ እምነት ባልንጀሮቹ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ፖሊሶቹ ከወንድም ኩትሰንኮ ምንም ዓይነት መረጃ እንደማያገኙ ሲገነዘቡ ለተጨማሪ ጥያቄ ወደ ምርመራ ክፍል ወሰዱት።
ወንድም ኩትሰንኮ ቺታ ውስጥ ቤታቸው ሲፈተሽ ከተያዙ ከሌሎች ሦስት ወንድሞች ማለትም ከሰርጌ ኪሪልዩክ፣ ከፓቬል ማማሊሞቭ እና ከቭላድሚር ዬርሞላይቭ ጋር በእስር እንዲቆይ ተደርጓል።
ከሁለት ቀናት በኋላ የኢንጎድስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ኩትሰንኮ፣ ወንድም ኪሪልዩክ እና ወንድም ማማሊሞቭ ለ72 ሰዓት በእስር እንዲቆዩ ወስኗል። ወንድም ዬርሞላይቭ ደግሞ ከእስር ቤት ወጥቶ በቁም እስር እንዲቆይ ፍርድ ቤቱ በይኗል።
መርማሪው፣ ወንድም ቫዲም ኩትሰንኮንና ሌሎቹን ሁለት ወንድሞች ለመክሰስ የሚያበቃ መረጃ ስላላቀረበ የካቲት 15 ሁሉም ከእስር ተለቅቀዋል። መርማሪው የወንድሞችን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ሳያቀርብና በእነሱ ላይ ምንም ዓይነት ገደብ እንዲጣልባቸው ሳያደርግ ሁሉንም ለቅቋቸዋል።
ወንድም ኩትሰንኮና በሩሲያ የሚኖሩ ሌሎች ወንድሞቻችን ይሖዋ በመከራቸው ሁሉ እንደሚደግፋቸው በመተማመን “ደፋርና ብርቱ” እንዲሆኑ እንጸልያለን።—ኢያሱ 1:7, 9