በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም አሌክሳንደር ሻሞቭ እና ባለቤቱ ናዴዥዳ፤ ወንድም አንድሬ ሼፒን እና ባለቤቱ ሴኒያ፤ ወንድም ዬቭጌኒ ኡድንሴፍ እና ባለቤቱ ዬሊዛቬታ

ሚያዝያ 29, 2021
ሩሲያ

በእምነታቸው ምክንያት ክስ የተመሠረተባቸው ወንድም ሻሞቭ፣ ወንድም ሼፒን እና ወንድም ኡድንሴፍ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ቀጥለዋል

በእምነታቸው ምክንያት ክስ የተመሠረተባቸው ወንድም ሻሞቭ፣ ወንድም ሼፒን እና ወንድም ኡድንሴፍ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ቀጥለዋል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት የቀረበለትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ

ታኅሣሥ 2, 2021 የኪሮቭ ክልል ፍርድ ቤት ወንድም አሌክሳንደር ሻሞቭ፣ ወንድም አንድሬ ሼፒን እና ወንድም ዬቭጌኒ ኡድንሴፍ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። በመሆኑም የተጣለባቸውን የገንዘብ ቅጣት መክፈል ይኖርባቸዋል። ሆኖም እስር ቤት አይገቡም።

ሐምሌ 19, 2021 በኪሮቭ ክልል የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ሻሞቭ፣ ወንድም ሼፒን እና ወንድም ኡድንሴፍ ጥፋተኛ ናቸው በማለት ወንድም ሻሞቭ 420,000 ሩብል (5,618 የአሜሪካ ዶላር)፣ ወንድም ሼፒን 500,000 ሩብል (6,688 የአሜሪካ ዶላር) እና ወንድም ኡድንሴፍ 200,000 ሩብል (2,675 የአሜሪካ ዶላር) ቅጣት እንዲከፍሉ ወስኗል።

አጭር መግለጫ

አሌክሳንደር ሻሞቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1960 (ኮማሮቮ፣ ኪሮቭ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ለወላጆቹ ከስድስት ልጆች አንዱ ነው። ልጅ ሳለ ወላጆቹን በሞት አጥቷል። ከስድስት ዓመቱ ጀምሮ በቤተሰቡ እርሻ ላይ ይሠራ ነበር። ካደገ በኋላ ከሙያ ኮሌጅ ተመርቆ ቴሌቪዥን በመጠገን ሥራ መተዳደር ጀመረ። በ1986 ከናዴዥዳ ጋር ትዳር መሠረተ። ለአካለ መጠን የደረሰች ሴት ልጅ አላቸው። ከዚህ በፊት ባጋጠመው የልብ ሕመም ምክንያት ቀዶ ሕክምና ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጥ የጡረታ አበል ይቀበላል። እሱና ናዴዥዳ በ1990ዎቹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። አሌክሳንደር በ2000 ተጠመቀ

አንድሬ ሼፒን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1991 (ኮሎሬቭ፣ ሞስኮ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ እውነትን የተማረው ከወላጆቹ ነው። በ2015 ከሴኒያ ጋር ትዳር መሠረተ። ሲቪል መሐንዲስ ሆኖ ይሠራል። በ2010 ተጠመቀ

ዬቭጌኒ ኡድንሴፍ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1949 (ኪሮቭ)

  • ግለ ታሪክ፦ ልጅ ሳለ ከባድ የልብ ሕመም ነበረበት። ሲቪል መሐንዲስ እና የብረታ ብረት ባለሙያ ነው። በ1970 ከዬሊዛቬታ ጋር ትዳር መሠረተ። በ1991 ሁለቱም ከዬሊዛቬታ እህት እውነትን ሰሙ። ለይሖዋ ያለው ፍቅር የሲጋራ እና የአልኮል መጠጥ ሱሱን እንዲያሸንፍ ረድቶታል። በ1996 ተጠመቀ

የክሱ ሂደት

መጋቢት 26, 2019 የሩሲያ ፖሊሶች በኪሮቭ የሚገኙ 12 የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ። ከፍተሻውና በወንድሞች ላይ ከተደረገው ከፍተኛ ክትትል በኋላ አቃቤ ሕጉ በአሌክሳንደር፣ በአንድሬና በዬቭጌኒ ላይ ክስ መሠረተ። አንድሬ ለሁለት ቀናት ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ። አቃቤ ሕጉ በተለመዱ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈልን እንደ “ጽንፈኝነት” ቆጥሮት ነበር። ወንድሞች ፈጽመዋቸዋል ከተባሉት የወንጀል ድርጊቶች መካከል መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና መዝሙር መዘመር ይገኙበታል።

ወንድሞች ይህን ፈተና ለመቋቋም በይሖዋ፣ በድርጅቱና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሙሉ እምነት ማሳደራቸውን ቀጥለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አሌክሳንደር በዕብራውያን ምዕራፍ 12 የተጠቀሱት “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” ስለተዉት ምሳሌ ማሰቡ እንዲበረታ ረድቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “በጥንት ዘመን የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች ለእምነታቸው ሲሉ ደፋር መሆንና መጽናት እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝበው ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታው ከባድ ሲሆንብኝ እነሱ በተዉት ምሳሌ ላይ አሰላስላለሁ። እነሱ ከዚህ የከፋ ጭካኔና ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ይህን ማስታወሴ ‘ለእምነት ብርቱ ተጋድሎ’ ማድረጌን እንድቀጥል ረድቶኛል።”—ይሁዳ 3

አንድሬ በናዚ ጀርመን እና በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የነበሩትን ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ማሰቡ አበረታቶታል። “ያሳዩት ድፍረት በጣም ያስገርመኛል” በማለት ተናግሯል። በተጨማሪም ይሖዋ ጸሎታቸውን የመለሰበትና ላሳዩት ታማኝነት ወሮታቸውን የከፈለበት መንገድ ያስደንቀዋል። ይህም የሚፈልገውን ነገር በቀጥታ ጠቅሶ ወደ ይሖዋ እንዲጸልይ አነሳስቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ድፍረት እንዲሰጠኝ ደግሜ ደጋግሜ ጸልያለሁ። . . . አሁን የምንኖረው ልዩ በሆነ ጊዜ ላይ እንደሆነ እናውቃለን። ያለንበት ሁኔታ ልዩ የአገልግሎት አጋጣሚዎችንና ልዩ ተሞክሮዎችን የምናገኝበት ብሎም በይሖዋ ላይ ለየት ያለ እምነት የምናሳድርበት አጋጣሚ ይሰጠናል።”

ሦስቱን ወንድሞቻችንንና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታችን እናስባቸዋለን። ይሖዋ እንደሚያጽናናቸው እንዲሁም ‘መልካም የሆነውን ነገር እንዲያደርጉና እንዲናገሩ እንደሚያጸናቸው’ እርግጠኞች ነን።—2 ተሰሎንቄ 2:17