በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም አንድሬ አንድሬዬቭ፣ ወንድም አርተም ባግራትያን እና ባለቤቱ እህት አሌቭቲና እንዲሁም ወንድም አንድሬ ሪሽኮቭ

መጋቢት 16, 2021
ሩሲያ

በኩርስክ ክልል አንድ ባልና ሚስት እንዲሁም ሦስት ወንድሞች በእምነታቸው ምክንያት ሊታሰሩ ይችላሉ

በኩርስክ ክልል አንድ ባልና ሚስት እንዲሁም ሦስት ወንድሞች በእምነታቸው ምክንያት ሊታሰሩ ይችላሉ

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት አምስት የይሖዋ ምሥክሮች ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ

ጥር 20, 2022 የኩርስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም አንድሬ አንድሬዬቭ፣ ወንድም አንድሬ ሪሽኮቭ፣ ወንድም አሌክሳንደር ቮስፒታንዩክ እንዲሁም ወንድም አርተም ባግራትያን እና ባለቤቱ አሌቭቲና ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። መጀመሪያ ላይ የተላለፈባቸው ብይን በዚያው ይጸናል።

ሰኔ 3, 2021 በኩርስክ የሚገኘው ኢንደስትሪያል አውራጃ ፍርድ ቤት በአንድ ባልና ሚስት እንዲሁም በሌሎች ሦስት ወንድሞች ላይ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ውሳኔ አስተላልፏል። ወንድም አንድሬዬቭ አራት ዓመት ተኩል፣ ወንድም ሪሽኮቭ ሦስት ዓመት፣ ወንድም ባግራትያን ሁለት ዓመት ተኩል፣ ባለቤቱ አሌቭቲና ደግሞ ሁለት ዓመት እንዲታሰሩ ተፈርዶባቸዋል። በዚሁ ክስ ላይ የተካተተው ወንድም ቮስፒታንዩክም ለሁለት ዓመት በክትትል ሥር እንዲቆይና የተለያዩ ገደቦች እንዲጣሉበት ተደርጓል።

አጭር መግለጫ

አንድሬ አንድሬዬቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1976 (ኩርስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ በ1999 ከስቬትላና ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለት ሴቶች ልጆች አሏቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ትንቢቶች መፈጸማቸውን ሲያውቅ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፍላጎት አደረበት። በ2002 ተጠመቀ

አሌቭቲና ባግራትያን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1977 (ኩርስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ በልጅነቷ ሥዕል ትወድ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረችው በልጅነቷ ነው። በ1997 ተጠመቀች። በ2012 ከአርተም ጋር ትዳር መሠረተች። የፀጉር ሥራ ባለሙያ ነበረች፤ እናቷንም ትንከባከብ ነበር

አርተም ባግራትያን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1972 (አቦቭያን፣ አርሜንያ)

  • ግለ ታሪክ፦ ወደ ሩሲያ የመጣው ከአርሜንያ ነው። ከአሌቭቲና ጋር በኩርስክ ተገናኙ። ባልና ሚስቱ ተፈጥሮን ይወዳሉ። አርተም የተጠመቀው በ2000 ነው

አንድሬ ሪሽኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1987 (ኩርስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ልጅ እያለ አባቱ ሞተበት። እናቱ ሁለት ሥራ ትሠራ ስለነበር አብዛኛውን የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ከአያቱ ጋር ነው። ለዓመታት ሲያሳስቡት ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ ካገኘ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ፈለገ። በ2011 ተጠመቀ። በ2016 ከማሪና ጋር ትዳር መሠረተ። ቀደም ሲል አፓርታማ በመጠገን ሥራ ተሰማርቶ ነበር

የክሱ ሂደት

ጥቅምት 16, 2019 የፌደራል ደህንነት አባላት በኩርስክ የሚገኙ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች የበረበሩ ሲሆን በወንድሞቻችን ላይ ምርመራ አካሂደው ነበር።ከዚያም ወንድም አንድሬ አንድሬዬቭ እንዲሁም ወንድም አርተም ባግራትያን እና ባለቤቱ በቁጥጥር ሥር ዋሉ። ጥር 21, 2020 ደግሞ ባለሥልጣናቱ ወንድም አንድሬ ሪሽኮቭን በቁጥጥር ሥር አዋሉት። እህት አሌቭቲና ባግራትያን ከ13 ወር በላይ ማረፊያ ቤት ከቆየች በኋላ ታኅሣሥ 17, 2020 ተለቀቀች። በአሁኑ ወቅት በቁም እስር ላይ ናት። ሦስቱ ወንድሞች አሁንም ማረፊያ ቤት ናቸው።

አርተም ባግራትያን የስኳር በሽተኛ ነው። አሌቭቲና እሷና ባለቤቷ ተለያይተው ስለታሰሩበት ወቅት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ለረጅም ጊዜ ያህል ስለ ደህንነቱ ማወቅ አልቻልኩም ነበር፤ ‘በሽታው ብሶበት ይሆን?’ የሚለው አሳስቦኝ ነበር። በጣም ናፍቆኝ ነበር።”

አሌቭቲና እሷም ሆነች ሌሎቹ ወንድሞች ማረፊያ ቤት በቆዩበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ እንደሚንከባከባቸው ምንጊዜም እርግጠኛ እንደነበረች ገልጻለች። እንዲህ ብላለች፦ “[ይሖዋ] ሁልጊዜም ያበረታኝ ነበር። አሁንም ይህን ማድረጉን እንደሚቀጥል አውቃለሁ። በእሱ ሙሉ በሙሉ እተማመናለሁ።”

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ይሖዋ ለሦስቱ ወንድሞቻችን እና ለእህታችን ምንጊዜም ጽኑ ግንብ እንደሚሆንላቸው እንተማመናለን።—ምሳሌ 18:10