በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭ፣ እህት ቨነራ ዱሎቫ እና ልጇ እህት ዳርያ ዱሎቫ፣ ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት

ጥር 24, 2020
ሩሲያ

በካርፒንስክ፣ ሩሲያ የሚኖሩ ሁለት እህቶችና አንድ ወንድም ፍርድ ይጠብቃቸዋል

በካርፒንስክ፣ ሩሲያ የሚኖሩ ሁለት እህቶችና አንድ ወንድም ፍርድ ይጠብቃቸዋል

የካርፒንስክ ከተማ ፍርድ ቤት ከእህት ቨነራ ዱሎቫ፣ ከእህት ዳርያ ዱሎቫ እና ከወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭ ጋር በተያያዘ በተመሠረተው ክስ ላይ ሰኞ፣ ጥር 27, 2020 ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል። አቃቤ ሕጉ በወንድም ፕሪያኒኮቭ እና በእህት ቨነራ ዱሎቫ ላይ የሦስት ዓመት እስር በገደብ፣ በእህት ዳርያ ዱሎቫ ላይ ደግሞ የሁለት ዓመት እስር በገደብ እንዲበየን ጠይቋል።

ሚያዝያ 19, 2016 ወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭና እህት ቨነራ ዱሎቫ አንድን ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አወያዩት። የሰውየው ዘመድ የሆነ አንድ ሰው፣ ወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭና እህት ቨነራ ዱሎቫ ሌቦች እንደሆኑ በመግለጽ ፖሊስ ጠራ። ሁለቱም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰዱ። ፖሊሶቹም ጽሑፎቻቸውን ወሰዱባቸው፤ አሻራቸውንም ተቀበሉ።

በዚህ ምክንያት ከሁለት ዓመታት በኋላ ለምርመራ በድጋሚ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰዱ። ፖሊሶቹም ስልካቸውንና ሌሎች የግል ሰነዶቻቸውን ወሰዱ። የፖሊስ አዛዡ በወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭና በእህት ቨነራ ዱሎቫ ስልክ ላይ ያለውን መረጃ አንድ የሥነ መለኮት ረዳት ፕሮፌሰር እንዲመረምር አደረገ። ፕሮፌሰሩ ያዘጋጀው የ15 ገጽ ሪፖርት በስልካቸው ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት እንደሚገኝ የሚገልጽ ነበር። ሪፖርቱን መሠረት በማድረግ በወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭና በእህት ቨነራ ዱሎቫ ላይ ክስ እንዲመሠረትባቸው ጥያቄ ቀረበ። ከዚያም የካርፒንስክ ከተማ ፍርድ ቤት፣ ፖሊሶች የወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭንና የእህት ቨነራ ዱሎቫን ቤት እንዲፈትሹ ፈቃድ ሰጠ።

የእህት ቨነራ ዱሎቫ ቤት በተፈተሸበት ወቅት ፖሊሶቹ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን፣ መጽሐፎችንና ፎቶግራፎችን ወሰዱ። የእህት ቨነራ ዱሎቫ ልጅ የሆነችው የ18 ዓመቷ ዳርያም ምርመራ ተደረገባት። ቀጥሎም ፖሊሶቹ የእህት ቨነራ ዱሎቫን ዘመዶች ቤት እንዲሁም የወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭን ቤት ፈተሹ።

ሚያዝያ 16, 2019 ደግሞ ሦስት የፌደራል ደህንነት ፖሊሶች፣ አንድ መርማሪና ሌሎች ሁለት ፖሊሶች የወንድም ፕሪያኒኮቭን ቤት በድጋሚ ፈተሹ። ፖሊሶቹ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችንና ሌሎች የግል ንብረቶችን ወስደዋል።

እህት ዳርያ ዱሎቫም ከእናቷና ከወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭ ክስ ጋር በተያያዘ እንደ ተጠርጣሪ ተቆጥራ ሐምሌ 23, 2019 ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተጠራች። በሦስቱም ላይ ክስ ተመሠረተባቸው፤ ከዚያም የፍርድ ሂደቱ መስከረም 2019 ጀመረ።

እነዚህን ሦስት የይሖዋ ምሥክሮችና ሩሲያ ውስጥ እስርና ፍርድ የሚጠብቃቸውን ወደ 300 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች አስመልክቶ በልበ ሙሉነት እንዲህ የሚል ጸሎት እናቀርባለን፦ “በእሱ በመታመናችሁ የተነሳ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተስፋ እንዲትረፈረፍላችሁ ተስፋ የሚሰጠው አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ።”—ሮም 15:13