በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ሉቢን ከባለቤቱ ጋር እንዲሁም ወንድም ኢሳኮቭ ከባለቤቱ ጋር

መስከረም 1, 2021
ሩሲያ

በጠና የታመሙ ሁለት የሩሲያ ወንድሞች የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ከማረፊያ ቤት ተለቀቁ

በጠና የታመሙ ሁለት የሩሲያ ወንድሞች የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ከማረፊያ ቤት ተለቀቁ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ለሩሲያ ባለሥልጣናት ጥያቄ ካቀረበ በኋላ ነሐሴ 28, 2021 ወንድም አሌክሳንደር ሉቢን እና ወንድም አናቶሊ ኢሳኮቭ ከማረፊያ ቤት ተለቀቁ። ሁለቱም ወንድሞች የአካል ጉዳተኞች ቢሆኑም ሩሲያ ውስጥ በኩርጋን ክልል ለአንድ ወር ተኩል በማረፊያ ቤት ቆይተዋል። ሆኖም ክሳቸው በፍርድ ቤት ከታየ በኋላ እስራት ሊበየንባቸው ይችላል።

ሐምሌ 13 እና 14, 2021 በኩርጋን ክልል የሚገኙ የደህንነት ኃይሎች በይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ የጅምላ ፍተሻ አካሄዱ። በዚያ ወቅት በቁጥጥር ሥር ከዋሉት በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል የ56 ዓመቱ ወንድም ኢሳኮቭ እና የ65 ዓመቱ ወንድም ሉቢን ይገኙበታል።

ወንድም ሉቢን ከባድ የደም ቧንቧ እክልና የደም ግፊት እንዲሁም በሰውነት ክፍሎቹ ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሕመም አለበት። በየቀኑ ለ16 ሰዓት ያህል እርጥበት ያለው ኦክስጅን መውሰድ ያለበት ከመሆኑም ሌላ የሕክምና እርዳታ ያስፈልገዋል፤ ሆኖም ይህን እንዳያገኝ ተከልክሏል። መራመድ ያስቸግረዋል፤ እንዲሁም ያለሰው እርዳታ መነሳት አይችልም። ባለቤቱ ታትያናም የአካል ጉዳተኛ ስትሆን አራት ጊዜ ስትሮክ አጋጥሟታል።

ወንድም ኢሳኮቭ የደም ካንሰር አለበት፤ ከዚህም ሌላ አከርካሪውና ጎድኑ ላይ ብዙ ስንጥቅ አለው፤ በዚህም ምክንያት የግድ ዊልቼር መጠቀም አለበት። ማረፊያ ቤት በመግባቱ የተነሳ የኬሞቴራፒ ሕክምናውን መከታተል አልቻለም። የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቱንም እንዳያገኝ ተከልክሏል። የሚያሳዝነው ወንድም ኢሳኮቭ ማረፊያ ቤት በነበረበት ወቅት ኮቪድ-19ም ይዞት ነበር።

ጠበቆቻቸው ሁለቱ ወንድሞች እንዲፈቱ ለሳምንታት ያህል ፍርድ ቤቱን ይግባኝ ሲጠይቁ የቆዩ ቢሆንም ምላሽ አላገኙም። ዳኞቹ ውሳኔ ያስተላለፉት በኩርጋን ክልላዊ ሆስፒታል የሚገኙት ሐኪሞች የሰጡትን ምሥክርነት መሠረት በማድረግ ነው፤ ሐኪሞቹ ወንድም ሉቢን እና ወንድም ኢሳኮቭ ከእስር ነፃ እንዲሆኑ የሚያደርግ ሕመም እንደሌለባቸው በመጻፍ እውነታውን ክደዋል።

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ኢሳኮቭ እና ወንድም ሉቢን ከማረፊያ ቤት ሲወጡ

ነሐሴ 8, 2021 ጠበቆቹ ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤትም በምላሹ በሩሲያ ፌዴሬሽን ለሚገኘው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ ጥያቄ አቀረበ። ነሐሴ 24, 2021 ሁለቱ ወንድሞች ወደ ኩርጋን ክልላዊ ሆስፒታል በድጋሚ ተላኩ። በዚህ ጊዜ ሐኪሞቹ ወንድም ሉቢን እና ወንድም ኢሳኮቭ ባለባቸው ሕመም ምክንያት ከእስር ነፃ ሊሆኑ እንደሚገባ ገለጹ።

ስደትና ሕመምን ተቋቁመው በታማኝነት ለጸኑት ለእነዚህ ሁለት ወንድሞቻችን እንጸልያለን። ይሖዋ ለእነሱ ‘ብርታቱን ማሳየቱን’ እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—2 ዜና መዋዕል 16:9