በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም አርሲን አቫንዬሶቭ ከእስር ተፈትቶ ባቡር ጣቢያ እናቱ ስትቀበለው

ጥቅምት 11, 2024
ሩሲያ

አርሲን አቫንዬሶቭ ከሩሲያ ወህኒ ቤት ተለቀቀ

አርሲን አቫንዬሶቭ ከሩሲያ ወህኒ ቤት ተለቀቀ

ጥቅምት 9, 2024 ወንድም አርሲን አቫንዬሶቭ ከሩሲያ እስር ቤት ተለቅቋል። ወንድም አርሲን ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ሐምሌ 29, 2021 የስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶበት ነበር። ከዚያም ይግባኝ በሚታይበት ወቅት ዳኛው የአርሲንን ፍርድ ወደ ሰባት ዓመት ቀየረው። ብይን ከመተላለፉ በፊት ማረፊያ ቤት ያሳለፋቸው ሁለት ዓመታት ታሳቢ ስለተደረጉ አሁን የእስራት ጊዜውን አጠናንቅቋል።

የአርሲን አባት ወንድም ቪልዬን አቫንዬሶቭ በተመሳሳይ ችሎት ጥፋተኛ ተብሎ ተበይኖበት ለስድስት ዓመታት ታስሯል። የካቲት 9, 2024 ቪልዬን ከእስር ተፈትቷል

አርሲን፣ ራሱን ለይሖዋ ሲወሰን ከገባው ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ያለው ቁርጠኝነት ብርታት ሰጥቶታል። ከመታሰሩ በፊት ለፍርድ ቤቱ በተናገረው የመጨረሻ ቃል እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ተስያለሁ። ሕይወቴን ለእሱ የሰጠሁ ሲሆን ይህንንም ያደረግሁት ከልቤ ነው። ስእለቴን ማጠፍ አልፈልግም፣ አልችልም እንዲሁም ፈጽሞ አላደርገውም።” አርሲን በአምላክ ላይ ያለው ጠንካራ እምነት ሊከስም እንደማይችል ተናግሯል። “እምነቴ አልተናጋም፤ እንዲያውም ይበልጥ ተጠናክሯል” ብሏል።

አርሲን ከቤተሰቡ ጋር በመቀላቀሉ ደስ ብሎናል፤ በእስር ላይ ስላሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አጥብቀን መጸለያችንንም እንቀጥላለን። “ልዩ ልዩ ፈተናዎች [ቢያስጨንቁንም]” እምነታችንና ጽናታችን በእጅጉ እንደሚክሰን ማወቃችን ያጽናናናል።​—1 ጴጥሮስ 1:6, 7