በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የሃይማኖት ምሁርና የሩሲያ ፌዴሬሽን አማካሪ የሆኑት ዶክተር ሰርጌይ ኢጎሬቪች ኢቫኔንኮ

ጥቅምት 18, 2019
ሩሲያ

አንድ ታዋቂ የሃይማኖት ምሁር በሳራቶቭ ለይሖዋ ምሥክሮች ተከራከሩ

አንድ ታዋቂ የሃይማኖት ምሁር በሳራቶቭ ለይሖዋ ምሥክሮች ተከራከሩ

መስከረም 4, 2019 በሳራቶቭ ከተማ የስድስት የይሖዋ ምሥክሮች ክስ በታየበት ወቅት፣ ታዋቂ የሃይማኖት ምሁርና የሩሲያ መንግሥት አማካሪ የሆኑት ሰርጌይ ኢጎሬቪች ኢቫኔንኮ በፍርድ ቤት ቀርበው ለይሖዋ ምሥክሮች ምሥክርነት እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር። ዶክተር ኢቫኔንኮ በሩሲያ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች በተመለከተ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች አዘጋጅተዋል። ከዚህ በታች የሰፈረው፣ ዶክተር ኢቫኔንኮ በፍርድ ቤት ውስጥ ከሰጡት ምሥክርነት ተቀንጭቦ የተወሰደ ሐሳብ ነው፦

የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወትና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ። “የይሖዋ ምሥክሮችን ለየት የሚያደርጋቸው አንድ ነገር አለ፦ ጥብቅ በሆኑ ሕጎች አይመሩም ወይም የትኛውንም መሪ አይከተሉም፤ ከዚህ ይልቅ ተከታዮቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሕሊናቸውን በማሠልጠን በፈቃደኝነትና በግለሰብ ደረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲያደርጉ ለመርዳት ይሞክራሉ።

“የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ክርስቶስና ተከታዮቹ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዳደረጉት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሰፈረውን ሐሳብ ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ።

“የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን አብረው በማጥናት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎችን በመመለስና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መዝሙሮችን በመዘመር አምላክን በኅብረት ማምለካቸው በሁሉም መስክ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ለመከተል ልዩ ጥረት እንደሚያደርጉ ያሳያል።

“በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች፣ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ መታቀፍ እንዳለባቸው ያምናሉ። ይህን የሚያምኑት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ ደቀ መዛሙርቱ የተገለጸውን ነገር እንዲሁም ክርስትና በጀመረበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። . . . የይሖዋ ምሥክሮች በጉባኤ ታቅፈው አምላክን በኅብረት ማምለክ እንዳለባቸው ያምናሉ።

“የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተለይተው የሚታወቁት በመካከላቸው ባለው ፍቅር እንደሆነ ጎላ አድርገው ይገልጻሉ።”

የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት እንቅስቃሴ። “የይሖዋ ምሥክሮች በስብከታቸው ተለይተው ይታወቃሉ። ስለ ስብከትና ስለ ቅንዓት ከተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚደርስ ሃይማኖት ያለ አይመስለኝም። ሁሉም አማኝ ጊዜ መድቦ መስበክ ይጠበቅበታል።

“በሚሰብኩበት ጊዜ በአብዛኛው ‘መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ላሳይህ’ ይላሉ። ከዚያም ግለሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን ራሱ አይቶ ማረጋገጥ ይችላል። በሐሳባቸው ከተስማማ ሃይማኖታቸውን ሊከተል ይችላል። ካልተስማማ ደግሞ ሃይማኖታቸውን አይቀበልም። የይሖዋ ምሥክሮች ማንም ሃይማኖታቸውን እንዲቀበል አያስገድዱም።”

የይሖዋ ምሥክሮች በጽንፈኝነት መከሰሳቸውን በተመለከተ። “መጀመሪያ ላይ፣ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ አንዳንድ ጽሑፎች ጽንፈኝነት የሚንጸባረቅባቸው እንደሆኑ ተገለጸ፤ ምክንያቱም እነዚህ ጽሑፎች ትክክለኛውን ሃይማኖት የያዙት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንደሆኑና ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ ስህተት መሆናቸውን እንደሚያስተምሩ አንዳንድ ባለሙያዎች ተናገሩ። እርግጥ ሌሎች ሃይማኖቶችም እንዲህ ብለው ያስተምራሉ፤ ሆኖም የተከሰሱት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች የእነሱ ሃይማኖት ብቻ እውነተኛ እንደሆነና ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ ሐሰተኛ እንደሆኑ መግለጻቸው ሃይማኖታዊ የበላይነት የሚንጸባረቅበት ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ታስቦ ነበር።

“የሃይማኖት ምሁር እንደመሆኔ መጠን [በፍርድ ቤቱ] ውሳኔ ላይ ድክመት ይታየኛል፤ ምክንያቱም የትኛውም ሃይማኖት፣ የራሱ ሃይማኖት ብቻ ትክክል እንደሆነ ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ ግን ስህተት እንደሆኑ ወይም እንደተታለሉ መግለጹ አይቀርም።

“የትኛውም ሃይማኖተኛ ሰው የራሱ ሃይማኖት ብቻ ሙሉ በሙሉ ትክክል እንደሆነ፣ ሌሎች ሃይማኖቶች ግን ሙሉ በሙሉ ወይም በአብዛኛው ሐሰት እንደሆኑ ያምናል። እንደዚያ ብሎ ካላመነ እንደ ግብዝ መቆጠሩ አይቀርም።

“ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ ሕግ ጋር እስካልተጋጨ ድረስ ለመንግሥት ሕግ ለመታዘዝ የቻሉትን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ። የይሖዋ ምሥክሮች የጠፋ የገንዘብ ቦርሳ እንደመለሱ እንዲሁም የሚጠበቅባቸውን ግብር ወይም ክፍያ በሐቀኝነት እንደከፈሉ የሚናገሩ ብዙ ዘገባዎችን የምንሰማው ያለምክንያት አይደለም። ከልባቸው ሐቀኞችና ሕግ አክባሪዎች ናቸው፤ ምንም ዓይነት የጽንፈኝነት ድርጊት አላየሁባቸውም።”

የይሖዋ ምሥክሮችና መጽሐፍ ቅዱስ። “የይሖዋ ምሥክሮችን ለየት የሚያደርጋቸው አንዱ ነገር ለግል ንባባቸው እንዲሁም ለአገልግሎታቸው የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን የሚጠቀሙ መሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በተለያዩ ቋንቋዎች ለማሰራጨት ልዩ ጥረት ያደርጋሉ። ለመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ትኩረት መስጠታቸው ከሌሎች ሃይማኖቶች የተለዩ ያደርጋቸዋል። እርግጥ እዚህ አገር ውስጥ የእነሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጽንፈኛ ተብሎ ተፈርጇል። . . . ይህ ውሳኔ እንዲተላለፍ ያደረጉት ሰዎች ምናልባት የይሖዋ ምሥክሮች ከዚያ ትርጉም ጋር ልዩ ትስስር እንዳላቸውና ያ መጽሐፍ ቅዱስ ከሌለ እንቅስቃሴያቸውን እንደሚያቆሙ አስበው ሊሆን ይችላል። ይህ ግን የተሳሳተ አመለካከት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።”

እምነታቸውን ለማራመድ የሚጠቀሙባቸውን ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ተቋማት በተመለከተ። “የሩሲያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ እንደሚያሳየው . . . አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ሕጋዊ እውቅና ያለው ተቋም አይጠቀሙም ነበር። . . . ከዚህ አንጻር በአንድ አካባቢ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ የአንድ ሕጋዊ ተቋም አባል ተደርገው ይቆጠራሉ የሚለው ሐሳብ ትክክል አይደለም።

“ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ተቋማትም ቢሆኑ . . . ቻርተራቸውን በጥንቃቄ ሳነብ እንደተረዳሁት በቻርተራቸው ላይ የበላይ ተመልካች፣ ሽማግሌ፣ አቅኚ እንደሚሉት ያሉ ቃላት አይገኙም። ቻርተሮቹ በአብዛኛው የሚጠቅሱት የተቋማቱን መሥራቾች ሲሆን እነሱም ከአሥር አይበልጡም። በሕጋዊ ሰነዶቹ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ኃላፊነታቸው ከሕግ ጋር የተያያዘ እንጂ ከሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ አይደለም። . . . በየትኛውም አገርም ሆነ አካባቢ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸው ተመሳሳይ ነው።

“የይሖዋ ምሥክሮች [ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሕጋዊ ተቋማቱን ብቻ ለማፍረስ ያደረገውን ውሳኔ] ላለመጣስ ጥንቃቄ በማድረግ ሕጉን አክብረዋል። ሆኖም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸውን ማከናወናቸውን ይቀጥላሉ፤ ምክንያቱም እገዳ የተጣለው በሃይማኖቱ ላይ አይደለም። በግለሰብ ደረጃ አምልኳቸውን መፈጸማቸውን ይቀጥላሉ። ይህን የማድረግ መብት እንዳላቸው ያምናሉ፤ እኔም የሃይማኖት ምሁር እንደመሆኔ መጠን ይህን ማድረጋቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚጥስ አይሰማኝም።”

የይሖዋ ምሥክሮችና ደም። “መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሰው ሕይወት የሚገኘው በደሙ ውስጥ’ እንደሆነ ይናገራል፤ በመሆኑም ደምን መብላት ተገቢ አይደለም። ጥቅሱ የሚናገረው ቃል በቃል ደምን ስለመብላት ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ሐሳብ የሚረዱት ሰፋ አድርገው ነው። ደምን ለምግብነት አይጠቀሙም (ለምሳሌ ደም የገባበት ቋሊማ አይበሉም)፤ እንዲሁም ለሕክምና ደም አይወስዱም። ሆኖም ንዑስ የደም ክፍልፋዮችን ለመውሰድ ፈቃደኛ ናቸው፤ በዚህ ረገድ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይችላል። . . . ደም የማይወስዱት መሞት ስለሚፈልጉ አይደለም፤ እንዲያውም ከሁሉ የተሻለው ሕክምና እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። እነሱም ሆኑ በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ደም መውሰድ ለኤድስ ወይም ለሌላ ሕመም ሊያጋልጥ ይችላል። ያለደም የሚደረግ ቀዶ ሕክምና የተሻለ ውጤት ያስገኛል፤ ደግሞም አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በርካታ ሀብታሞች ያለደም ቀዶ ሕክምና ቢደረግላቸው ይመርጣሉ፤ ምክንያቱም ይህ ዘዴ ለተለያዩ በሽታዎች ከመጋለጥ ያድናቸዋል።”

የይሖዋ ምሥክሮችና መዋጮ። “አንድ ሰው ምንም መዋጮ ላለመስጠት ሊመርጥ ይችላል። ምናልባትም አንድ ሰው ዕድሜ ልኩን በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ቢገኝም አንድም ሩብል ወይም ዶላር መዋጮ ላያደርግ ይችላል። መዋጮ ማድረግ ወይም አለማድረግ የእያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ ነው።”

ዶክተር ኢቫኔንኮ የይሖዋ ምሥክሮች ለእምነታቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሕግ አክባሪ ዜጎች መሆናቸውን ጎላ አድርገው ቢገልጹም ፍርድ ቤቱ የእሳቸውን ሐሳብ ችላ በማለት በስድስቱም ወንድሞች ላይ እስር በይኖባቸዋል።

ሩሲያ በወንድሞቻችን ላይ የሐሰት ክስ መሰንዘሯንና እነሱን ማሰሯን ብትቀጥልም ይሖዋ ደፋርና ታማኝ ወንድሞቻችንን እንዲባርካቸውና ሞገሱን እንዲያሳያቸው መጸለያችንን እንቀጥላለን።—መዝሙር 109:2-4, 28