በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ላሪሳ አርታሞኖቫ

የካቲት 15, 2021
ሩሲያ

እህት ላሪሳ አርታሞኖቫ በእምነቷ ምክንያት ተፈረደባት

እህት ላሪሳ አርታሞኖቫ በእምነቷ ምክንያት ተፈረደባት

የፍርድ ውሳኔ

ሩሲያ ውስጥ በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት፣ የእህት ላሪሳ አርታሞኖቫን ጉዳይ ተመልክቶ የካቲት 12, 2021 ውሳኔውን አሳውቋል። እህት ላሪሳ እስከ ስድስት ዓመት የሚደርስ እስራት ሊፈረድባት ይችላል የሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ 10,000 ሩብል (135 የአሜሪካ ዶላር) እንድትቀጣ ወስኗል።

አጭር መግለጫ

ላሪሳ አርታሞኖቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1970 (ቢሮቢድዣን፣ የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ የሦስት ዓመት ልጅ ሳለች አባቷ በሰው እጅ ሕይወቱ አለፈ። ላሪሳ ኬክ ጋጋሪ፣ ግራፊክ ዲዛይነር እና ልብስ ሰፊ ሆና ሠርታለች። በ1990 ትዳር መሠረተች። ዬቭጌኒ የተባለ ልጅ አላት፤ ልጇ ብዙም የማያጋጥም የጤና እክል አለበት። ላሪሳም የመገጣጠሚያ ሕመም አለባት። ታማሚ ብትሆንም እንቅስቃሴ ማድረግ ያስደስታታል። ብስክሌት መንዳት፣ የበረዶ ላይ ሸርተቴ መጫወት እንዲሁም ሥዕል መሣል ትወዳለች

    በዓለም ላይ ስለሚታየው ግፍ፣ ሐዘንና ክፋት የተፈጠሩባት ጥያቄዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና አነሳሷት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለጥያቄዎቿ አጥጋቢ መልስ በማግኘቷ በ1995 ተጠመቀች

የክሱ ሂደት

የሩሲያ ባለሥልጣናት መስከረም 25, 2019 በእህት ላሪሳ አርታሞኖቫ ላይ የወንጀል ክስ መሠረቱባት። ልጇም ለብቻው የወንጀል ክስ ተመሥርቶበታል። “በጽንፈኛ” ድርጅት እንቅስቃሴ ተካፍለዋል የሚል ክስ ከተመሠረተባቸው በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኙት 22 የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ላሪሳና ልጇ ይገኙበታል።

እናቷና እንጀራ አባቷ፣ ላሪሳ በእምነቷ ምክንያት የስድስት ዓመት እስራት ሊፈረድባት የነበረ መሆኑን ሲሰሙ በጣም ተገርመዋል፤ ምክንያቱም የላሪሳን አባት የገደለው ሰውም የተፈረደበት የስድስት ዓመት እስራት ነበር።

በቢሮቢድዣን በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚደርሰው ስደት ከመጀመሩ በፊት ላሪሳና ልጇ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አገልግሎት ለማሳደግ ጥረት አድርገው ነበር። ላሪሳ እንዲህ ብላለች፦ “በይሖዋ አገልግሎት መጠመድ እንዲሁም የራሳችንንና የቤተሰባችንን መንፈሳዊነት ማጠናከር በፍርሃት እንዳንሸነፍ ይረዳናል። ሰይጣን አሳዳጆቻችንን በመጠቀም፣ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ነፃነታችንን እንደሚያሳጣን እንድናስብ ለማድረግ ይሞክራል። በአንጻሩ ግን ይሖዋ እውነተኛ ነፃነት የምናገኘው እሱ ያስተማረንን ነገር በሥራ ላይ በማዋል እንደሆነ አረጋግጦልናል።”

በቢሮቢድዣን ክስ የተመሠረተባቸው 22 ወንድሞችና እህቶች፣ ይሖዋ እነሱ በሚያሳዩት ታማኝነት እንደሚደሰት እርግጠኞች ናቸው፤ እንዲሁም ሰይጣን ለሚሰነዝረው ስድብ መልስ እየሰጡ ነው።—ምሳሌ 27:11