በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ናታሊያ ክሪገር ከባለቤቷ ቫሊሪ ጋር

የካቲት 25, 2021
ሩሲያ

እህት ናታሊያ ክሪገር “የፍርድ ቀን” በተባለው የፍተሻ ዘመቻ የተነሳ ሊፈረድባት ይችላል

እህት ናታሊያ ክሪገር “የፍርድ ቀን” በተባለው የፍተሻ ዘመቻ የተነሳ ሊፈረድባት ይችላል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኙን ውድቅ አደረገ

ኅዳር 25, 2021 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው ፍርድ ቤት የእህት ናታሊያ ክሪገርን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል። መጀመሪያ የተላለፈባት ፍርድ በዚያው ይጸናል። እርግጥ አሁን ወህኒ አትወርድም።

ሐምሌ 30, 2021 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት እህት ናታሊያ ክሪገር ጥፋተኛ ናት የሚል ውሳኔ አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ በእህት ናታሊያ ላይ የሁለት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት ፈርዶባታል።

አጭር መግለጫ

ናታሊያ ክሪገር

  • የትውልድ ዘመን፦ 1978 (ካባረቭስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ እናቷ የሞተችው ናታሊያ ሕፃን እያለች ነው። በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋም ውስጥ ኖራለች። ስድስት ዓመት ሲሆናት 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው አሞርዝዬት፣ ሩሲያ ሄደች። በዚያም የይሖዋ ምሥክር ከሆኑት አያቷ፣ አክስቷ እና የአክስቷ ልጅ ጋር ኖራለች። ሥራዋ አረጋውያንን መንከባከብ ነው

  • በ1999 ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። በ2017 ከቫሊሪ ጋር ትዳር መሠረተች። እሷና ባለቤቷ መደነስ፣ በጀልባ መንሸራሸር እንዲሁም ተራራ መውጣት ይወዳሉ

የክሱ ሂደት

ግንቦት 2018 የሩሲያ ባለሥልጣናት የናታሊያ እና የቫሊሪን ቤት ፈተሹ። ይህ ፍተሻ የመንግሥት ባለሥልጣናት “የፍርድ ቀን” ብለው የሰየሙት የፍተሻ ዘመቻ ክፍል ነው። ከፍተሻው በኋላ አቃቤ ሕጉ በቫሊሪ ላይ የወንጀል ክስ መሠረተ። የካቲት 6, 2020 ደግሞ ባለሥልጣናቱ በናታሊያ ላይ የወንጀል ክስ መሠረቱ። ናታሊያ በዚያ ዕለት ከተከሰሱት ስድስት እህቶች አንዷ ናት።

ናታሊያ ከተመሠረተባት የወንጀል ክስ በተጨማሪ በአያቷ ሞት ምክንያት ከባድ ሐዘን ደርሶባታል፤ አያቷ የሞቱት የካቲት 2020 ነው። ናታሊያ አያቷን ለስድስት ዓመት ያህል ተንከባክባለች።

ናታሊያ እነዚህን መከራዎች እንድትቋቋም የረዳት ከይሖዋ ጋር ያላት ጠንካራ ወዳጅነት ነው። እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ሌሎች መጸለዬ በራሴ ችግሮች ላይ እንዳላተኩር ረድቶኛል። የደረሰብኝ ስደት ይሖዋ ይበልጥ እውን እንዲሆንልኝ እና ወደ እሱ ይበልጥ እንድቀርብ ረድቶኛል። ጸሎቶቼን እንደሚመልስኝ እና እንደሚደግፈኝ ተመልክቻለሁ።”

ናታሊያ፣ ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚደግፋት እንድትተማመን ባደረጓት ምክንያቶች ላይ አዘውትራ ታሰላስላለች። እንዲህ ብላለች፦ “በመዝሙር 94:19 ላይ የሚገኘው ‘አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ’ የሚለው ሐሳብ በጣም ያበረታኛል። ደፋር የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ስደት ቢደርስባቸውም እንደጸኑ የሚያሳዩ በርካታ ጥንታዊም ሆነ ዘመናዊ ምሳሌዎች አሉ። በእነዚህ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰሌ ተጨማሪ ብርታት ሰጥቶኛል።”