በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ኤሌና ባርማኪና እና ባለቤቷ ዲሚትሪ

መስከረም 28, 2020
ሩሲያ

እህት ኤሌና ባርማኪና በመጸለይዋ እና መጽሐፍ ቅዱስ በማንበቧ ክስ ተመሥርቶባታል

እህት ኤሌና ባርማኪና በመጸለይዋ እና መጽሐፍ ቅዱስ በማንበቧ ክስ ተመሥርቶባታል

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

በቭላዲቮስቶክ የሚገኘው የፐርቮርቸንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት፣ መስከረም 29, 2020 a በእህት ኤሌና ባርማኪና ጉዳይ ላይ ብይን እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል። እህት ባርማኪና የሦስት ዓመት እስር በገደብ ሊፈረድባት ይችላል። እህታችን ብይን እየተጠባበቀች ባለችበት በዚህ ጊዜ በባለቤቷ በዲሚትሪ ላይ የተመሠረተው ክስ እንደቀጠለ ነው።

አጭር መግለጫ

ኤሌና ባርማኪና

  • የትውልድ ዘመን፦ 1967 (ቼረፓኖቮ፣ ኖቮሲቢሪስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በዕድሜ የገፉ ወላጆቿንና አያቷን ትንከባከባለች። ፎቶግራፍ ማንሳት በጣም ስለምትወድ ፎቶ አንሺ ሆናለች። መዋኘትና ተራራ መውጣት ትወዳለች

  • ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች የአምላክን ኃይል እንደሚያሳዩ እርግጠኛ ሆነች። ይሖዋ ጸሎቷን ሲመልስላት እምነቷ ይበልጥ እየተጠናከረ ሄደ። በ2006 ከዲሚትሪ ጋር ትዳር መሠረተች

የክሱ ሂደት

ሐምሌ 28, 2018 ከጠዋቱ 1:00 ሰዓት ላይ መሣሪያ የታጠቁና ጭምብል ያጠለቁ ፖሊሶች 90 ዓመት የሆናቸው የእህት ኤሌና ባርማኪና አያት የሚኖሩበትን ቤት ሰብረው ገቡ። በወቅቱ እህት ባርማኪናና ባለቤቷ ዲሚትሪ አያትየውን ለመንከባከብ እዚያው ነበሩ። ወንድም ዲሚትሪ ከተያዘ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ታሰረ። ፖሊሶቹ “አንቺም ተራሽን ጠብቂ!” በማለት በእህት ባርማኪና ላይ ዛቱባት።

ከአንድ ዓመት በኋላ ባለሥልጣናቱ እህት ባርማኪና የባንክ ሒሳቧን እንዳታንቀሳቅስ አገዱባት። ነሐሴ 6, 2019 የፖሊስ መርማሪው እህት ባርማኪና በመጸለይዋ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በማንበቧና ስብከቶችን በማዳመጧ የወንጀል ክስ መሠረተባት። ጠበቃዋ፣ እህት ባርማኪና የአምልኮ ሥርዓት ከመፈጸም የተለየ ነገር እንዳላደረገች በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ክሱን እንዲያቋርጥ ጠየቀ። ዳኛው ግን የእህት ባርማኪና ድርጊት በሩስያ ሕግ በሚከለከለው “የጽንፈኝነት እንቅስቃሴ” ውስጥ የሚመደብ እንደሆነ በመናገር ከአቃቤ ሕጉ ጋር ወገኑ።

እህት ባርማኪና በወንጀል ክሱ የተነሳ ከፍተኛ ስሜታዊ ሥቃይና አካላዊ እንግልት ደርሶባታል። ባለቤቷ ከፍርድ በፊት በመታሰሩ ለ447 ቀናት ከእሱ ጋር ተለያይታ ኖራለች። እህት ባርማኪና ሥራ መቀጠርም በጣም ከባድ ሆኖባታል፤ ምክንያቱም ለፍርድ ቤት ቀጠሮ ወይም ለምርመራ ከተጠራች መገኘት ይጠበቅባታል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አቋማቸውን እንዲያላሉ ለማድረግ የሩሲያ ባለሥልጣናት እነሱን ‘በኃይል መጋፋታቸው’ አያስገርመንም። ሆኖም ይሖዋ ምንጊዜም ‘መጠለያና ብርታት’ እንደሚሆናቸው ማወቃችን ያጽናናናል።—መዝሙር 118:13, 14

a ቀኑ ሊቀየር ይችላል