በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ኦልጋ ኢቫኖቫ ከእስር ስትፈታ፤ የስምንት ዓመት እስር ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው ባለቤቷ ዬቭጌኒ የላከላትን እቅፍ አበባ ይዛ

ሰኔ 13, 2024
ሩሲያ

እህት ኦልጋ ኢቫኖቫ ከእስር ተፈታች

እህት ኦልጋ ኢቫኖቫ ከእስር ተፈታች

ሰኔ 11, 2024 እህት ኦልጋ ኢቫኖቫ፣ በዜሌኖኩምስክ ከተማ ከሚገኝ እስር ቤት ተለቀቀች። ጥቅምት 25, 2021 ጥፋተኛ ተብላ የሦስት ዓመት ተኩል እስራት ተፈርዶባት እንደነበር ይታወሳል። ከመታሰሯ በፊት በቁም እስር ያሳለፈችው አንድ ዓመት ከአራት ወር ታሳቢ ተደርጎ የፍርድ ጊዜዋ ተጠናቅቋል። በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ጥፋተኛ የተባለው ባለቤቷ ዬቭጌኒ የስምንት ዓመት እስራት ተፈርዶበት አሁን በእስር ላይ ነው።

ኦልጋ ከእስር በተፈታችበት ቀን ወዳጅ ዘመዶቿ ሲቀበሏት

ኦልጋ እስር ቤት በቆየችባቸው ጊዜያት በሳምንት ለስድስት ቀናት፣ በቀን ለ12 ሰዓታት ከባድ የጉልበት ሥራ እንድትሠራ ይጠበቅባት ነበር። በሩሲያ የተለያዩ ክፍሎች ወደሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች በተደጋጋሚ ተዘዋውራለች። ይህም ባለቤቷን በሞት ላጣችው ለኦልጋ እናት ለስቬትላና ልጇን መጠየቅ ከባድ አድርጎባታል። ስቬትላና ይሖዋ እንዴት እንደደገፋቸው ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ኦልጋ በተዛወረችበት ከተማ ሁሉ የአካባቢው ወንድሞችና እህቶች በፍቅር ተንከባክበዋታል። ስንቅና የሚያስፈልጓትን ነገሮች ለማቀበል ለሰዓታት ይሰለፋሉ፤ እንዲሁም በቻሉት አጋጣሚ ሁሉ ሄደው ይጠይቋታል። እኔ ልጠይቃት በምሄድበት ጊዜ ደግሞ ሁሌም የማርፍበት ቦታ ያዘጋጁልኛል፤ እንዲሁም በሚያስፈልገኝ ሁሉ ያግዙኛል። የማይረሳ ተሞክሮ ነው!”

ኦልጋ እና ባለቤቷ ዬቭጌኒ ከመታሰራቸው በፊት

ኦልጋ እስር ቤት በነበረችበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ላደረገላት ልዩ እንክብካቤ አመስጋኞች ነን። በእሷ መፈታት ተደስተናል፤ ለባለቤቷና በእስር ላሉት ሌሎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጸለያችንን እንቀጥላለን። ይሖዋ ታማኝ ፍቅር እንደሚያሳያቸውም እንተማመናለን።​—ዘፍጥረት 39:21