በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ኦልጋ ጋኑሻ

ሰኔ 23, 2021
ሩሲያ

እህት ኦልጋ ጋኑሻ ስደትን በጽናት ለመቋቋም ጸሎት ረድቷታል

እህት ኦልጋ ጋኑሻ ስደትን በጽናት ለመቋቋም ጸሎት ረድቷታል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኟን ውድቅ አደረገ

መስከረም 30, 2021 የሮስቶቭ ክልላዊ ፍርድ ቤት እህት ኦልጋ ጋኑሻ ያቀረበችውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። መጀመሪያ ላይ የተላለፈባት ብይን በዚያው ይጸናል። እርግጥ በአሁኑ ወቅት ወህኒ አትወርድም።

ሐምሌ 13, 2021 በሮስቶቭ ኦን ዶን የሚገኘው የቮሮሺሎቭስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት በእህት ኦልጋ ጋኑሻ ላይ የሁለት ዓመት የገደብ እስራት በይኖባታል።

አጭር መግለጫ

ኦልጋ ጋኑሻ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1961 (ሮስቶቭ ኦን ዶን፣ ሮስቶቭ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ወንድ ልጇን ብቻዋን ያሳደገች ሲሆን ከሥራዋ ጡረታ ወጥታለች። የእጅ ሥራ፣ ክላሲካል ሙዚቃ ማዳመጥና መጽሐፍ ማንበብ ትወዳለች

  • መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተነሳሳችው ከሞት ከተነሱ ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን ጋር በገነት የመኖር ተስፋ እንዳለን ስታውቅ ነው። በ1995 ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች

የክሱ ሂደት

በ2019 መጀመሪያ ላይ የሩሲያ ባለሥልጣናት በእህት ኦልጋ ጋኑሻ ቤት ውስጥ የድምፅ እና የቪዲዮ መቅረጫ መሣሪያ በድብቅ አስቀመጡ። በዚህ መንገድ ያገኙትን መረጃ እንደ ማስረጃ በመጠቀም ሰኔ 2019 ቤቷን በረበሩ። ባለሥልጣናቱ የግል ማስታወሻዎቿን፣ ደብዳቤዎቿንና ቡክሌቶቿንም አንብበዋል። ኦልጋ ነሐሴ 17, 2020 ክስ ተመሠረተባት፤ የፍርድ ሂደቱ መጋቢት 4, 2021 ተጀመረ። ከተከሰሰችባቸው “ወንጀሎች” መካከል ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች ቤቷ እንዲካሄዱ መፍቀድና በስብሰባዎቹ ላይ መካፈል እንዲሁም ስለ እምነቷ ለሌሎች መናገር ይገኙበታል። የእህት ሊዩድሚላ ፖኖማሬንኮ እና የእህት ገሊና ፓርኮቫ ጉዳይም ከእሷ ክስ ጋር አብሮ ሲታይ የነበረ ቢሆንም አሁን ጉዳያቸው ለየብቻ እየታየ ነው።

ለሁለት ዓመት የሚጠጋ ጊዜ በወሰደው የምርመራና የፍርድ ሂደት ወቅት ኦልጋን ያበረታታት የምትፈልገውን ነገር ለይታ ከልቧ መጸለይዋ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “የአምላክ ስም እንዲቀደስ በየዕለቱ አጥብቄ እጸልያለሁ። በተጨማሪም በማረፊያ ቤት፣ በእስር ቤትና በቁም እስር ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምሥክርነት መስጠት እንዲችሉና ውስጣዊ ጥንካሬ እንዲያገኙ እጸልያለሁ። ከዚህም ሌላ በይሖዋ ላይ የማይናወጥ እምነት እንዲኖራቸው እንዲሁም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን እሱ ፈጽሞ እንደማይተወን እንዲተማመኑ እጸልያለሁ።” ስለ ራሷ ስትናገር ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ፍርሃቴን ለማሸነፍና በእሱ ላይ ለመተማመን እንዲረዳኝ እንዲሁም ልክ ለኤርሚያስ እንዳደረገለት እኔንም የብረት ዓምድና የመዳብ ቅጥር እንዲያደርገኝ እለምነዋለሁ። ልክ እንደ ሦስቱ ዕብራውያን እሳት መሰል ፈተናዎችን በሙሉ በጽናት መቋቋም እፈልጋለሁ። ደግሞም ክርስቶስ በጠላቶቹ ፊት እንዳደረገው እኔም ምንጊዜም ክብሬን መጠበቅ እንደምችል ተስፋ አደርጋለሁ።”

ይሖዋ ኦልጋን ጨምሮ በእምነታቸው ምክንያት እየተሰደዱ ያሉ ክርስቲያኖችን ‘በጽድቅ ቀኝ እጁ’ መደገፉን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—ኢሳይያስ 41:10