በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት የሌና ረይኖ-ቸርኒሾቫ

ጥር 28, 2021
ሩሲያ

እህት የሌና ረይኖ-ቸርኒሾቫ በእምነቷ ምክንያት ሊፈረድባት ይችላል

እህት የሌና ረይኖ-ቸርኒሾቫ በእምነቷ ምክንያት ሊፈረድባት ይችላል

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

ሩሲያ ውስጥ በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት በእህት የሌና ረይኖ-ቸርኒሾቫ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ጥር 29, 2021 a ቀጠሮ ይዟል። አቃቤ ሕጉ በእህት የሌና ላይ እንዲተላለፍ የሚፈልገውን ብይን ገና አላሳወቀም።

አጭር መግለጫ

የሌና ረይኖ-ቸርኒሾቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1968 (ማሎይ፣ ኢርኩትስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በ1990ዎቹ ዓመታት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጠናች። ይህም ከጦር ሠራዊቱ እንድትወጣና የትዳር ሕይወቷን ለማሻሻል እንድትጥር አነሳሳት። በ1998 ተጠመቀች

  • ባለቤቷ የይሖዋ ምሥክር ባይሆንም ይሖዋን ለማገልገል ያደረገችውን ውሳኔ ይደግፋል። የሌና፣ እግር ኳስ እና መረብ ኳስ መጫወት ትወዳለች

የክሱ ሂደት

መስከረም 29, 2019 የቢሮቢድዣን ባለሥልጣናት በእህት የሌና ረይኖ-ቸርኒሾቫ ላይ የወንጀል ክስ መሠረቱ።

የሚያስፈሩ የፌዴራል ደህንነት አባላት የየሌናን ቤት በረበሩ። የሌና በወቅቱ እንድትረጋጋ የረዳት ይሖዋ እንደሆነ ትናገራለች። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ መረጋጋት እና ድፍረት እንዲሰጠኝ እንዲሁም ለእሱ ታማኝ እንድሆን እንዲረዳኝ ደጋግሜ ጸለይኩ። ፍተሻው የተካሄደው በተረጋጋ መንገድ ነበር፤ ሁሉም ሥርዓታማ ነበሩ።”

የፍርድ ሂደቱ በየሌና እና በቤተሰቧ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። ባለቤቷ ሐምሌ 2020 ለሦስተኛ ጊዜ የልብ ድካም አጋጠመው። ባለሥልጣናቱ የሌና ከቢሮቢድዣን ክልል እንዳትወጣ ከልክለዋታል። የባንክ ሒሳቧንም አግደውታል።

የሌና፣ ሌሎች የይሖዋ አገልጋዮች የደረሰባቸውን ስደት እንዴት እንደተቋቋሙ ማሰቧ ብርታት ሰጥቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ቤታቸው ስለተበረበረባቸው እንዲሁም በይሖዋ ላይ ባላቸው እምነት ምክንያት ስደት ስለደረሰባቸው ወንድሞች እና እህቶች የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ማንበብ እወዳለሁ። ብዙ ችግርና ግፍ ቢደርስባቸውም ሁሉንም ነገር በድፍረት ተቋቁመውታል።” የሌና አዘውትራ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቧና ባነበበችው ላይ ማሰላሰሏም ጠቅሟታል።

የሌና በአቋሟ ለመጽናት የወሰነች ሲሆን በኢሳይያስ 30:15 ላይ ማሰላሰል ያስደስታታል። ጥቅሱ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።” የሌና እንዲህ ብላለች፦ “ይህን ጥቅስ ሁልጊዜ አስታውሰዋለሁ። ይሖዋ ወደ ራሱ ስለሳበኝ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆንኩ ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል! . . . ምንጊዜም ውስጣዊ ሰላም አለኝ። ከምንጊዜውም ይበልጥ [በይሖዋ] እታመናለሁ እንዲሁም በሁሉም ነገር በእሱ እተማመናለሁ። ፈጽሞ እንደማይተወኝ እርግጠኛ ነኝ።”

a ቀኑ ሊቀየር ይችላል።