በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ዩሊያ ካጋኖቪች

የካቲት 11, 2021
ሩሲያ

እህት ዩሊያ ካጋኖቪች አስቀድማ መዘጋጀቷ ለመጽናት ረድቷታል

እህት ዩሊያ ካጋኖቪች አስቀድማ መዘጋጀቷ ለመጽናት ረድቷታል

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት በእህት ዩሊያ ካጋኖቪች ላይ ከተመሠረተው ክስ ጋር በተያያዘ የካቲት 18, 2021 a ውሳኔውን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል። አቃቤ ሕጉ እንዲተላለፍ የሚፈልገውን ብይን ገና አላሳወቀም።

አጭር መግለጫ

ዩሊያ ካጋኖቪች

  • የትውልድ ዘመን፦ 1966 (ሚካይሎቭካ፣ ቮልጎግራድ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ያጠናችው የሲቪል ምሕንድስና ነው። በወጣትነቷ ዳንስ ትማር ነበር፤ ከሙዚቃ ትምህርት ቤት ተመርቃለች፤ ኦርኬስትራ ውስጥ የሙዚቃ መሣሪያ ትጫወት ነበር፤ እንዲሁም የመዘምራን ቡድን አባል ነበረች። ባለቤቷ አሌክሳንደር የይሖዋ ምሥክር አይደለም፤ ሆኖም ዩሊያን ይደግፋታል እንዲሁም የወንጀል ክስ የተመሠረተባት መሆኑ ኢፍትሐዊ እንደሆነ ይሰማዋል

    ዩሊያ የምትቀርባቸውን ሰዎች በሞት ማጣቷ ስለ ሕይወት ትርጉም እንድታስብ አደረጋት። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ ውስጣዊ ሰላምና ተስፋ እንድታገኝ ረዳት። በ1998 ተጠመቀች። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተሏ ትዳሯን ለማጠናከር፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻልና ልጇን አርተርን ጥሩ አድርጋ ለማሳደግ ረድቷታል፤ አርተርም የይሖዋ ምሥክር ነው

    የጤና ችግር አለባት፤ ክስ የተመሠረተባት መሆኑ ደግሞ የጤና ችግሯን እያባባሰው ነው

የክሱ ሂደት

እህት ዩሊያ ካጋኖቪች እንዲህ ብላለች፦ “በማለዳ ቤቴ ሲንኳኳ የመጣው ማን እንደሆነ ወዲያውኑ ገብቶኝ ነበር። ልቤ በኃይል መምታት ጀመረ፤ ደጋግሜ ‘ይሖዋ እርዳኝ። ይሖዋ እርዳኝ’ እል ነበር።”

የሩሲያ ከተማ በሆነችው በቢሮቢድዣን የምትኖረው የ53 ዓመቷ እህታችን ያጋጠማት ሃይማኖታዊ ስደት የጀመረው ጥቅምት 10, 2019 ነው። የዩሊያ ቤት የተበረበረው የፌደራል ደህንነት (FSB) አባላት በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ከ20 የሚበልጡ ወንድሞችንና እህቶችን ቤት በበረበሩበት ወቅት ነው።

የተካሄደው ፍተሻ በጣም አስጨናቂ ነበር፤ ሆኖም ዩሊያም ሆነች ሌሎቹ የይሖዋ ምሥክሮች አስቀድመው መዘጋጀታቸው ብርታት ሰጥቷቸዋል።

ዩሊያ እንዲህ ብላለች፦ “ቤታችን ሊበረበር ስለሚችል አስቀድመን መዘጋጀት እንዳለብን በስብሰባ ላይ በተደጋጋሚ ይነገረን ነበር። እንዲህ ያለ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ስላወቅኩ ምን እንደማደርግና ምን እንደምናገር በማሰብ የአእምሮ ዝግጅት አድርጌ ነበር። አስቀድሞ መዘጋጀት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ገብቶኝ ነበር። በመሆኑም ከመደናገጥና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ከመጋባት ይልቅ ጥርት አድርጌ ማሰብ ችያለሁ።”

እንደሚጠበቀው ከፍተሻው በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሩሲያ ባለሥልጣናት ክስ መሠረቱ። ዩሊያና ሌሎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ‘በጽንፈኝነት እንቅስቃሴ ተካፍለዋል’ የሚል ክስ ተመሠረተባቸው።

መጋቢት 3, 2020 ባለሥልጣናቱ ክሱን ወደ ቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት መሩት። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የፍርድ ሂደቱ ለአምስት ወር ተቋረጠ። ከዚያም ዩሊያ ጥቅምት 22, 2020 በድጋሚ ፍርድ ቤት ቀረበች።

ዩሊያ እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ በኩል ሁኔታው አሳዝኖኝ ነበር። በሌላ በኩል ግን ለይሖዋ ሉዓላዊነት ጥብቅና መቆም በመቻሌ በጣም ተደስቼ ነበር።

ኢሳይያስ 41:10 በጣም ጠቅሞኛል። ይሖዋ የሰጠኝን ማጽናኛ ሁልጊዜ ማስታወስ እንድችል ጥቅሱን አትሜ ግድግዳ ላይ ሰቀልኩት። ይሖዋ ጉልበቴን እንዳበረታልኝ ተሰምቶኛል።”

ዩሊያ በርካታ ጥቅሶችን በቃሏ ለመያዝ ጥረት አድርጋ ነበር፤ ይህም አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም እንኳ እንድትረጋጋ እንዲሁም ደፋርና ደስተኛ እንድትሆን ረድቷታል።

ሁላችንም ወደፊት ለሚያጋጥሙን ፈተናዎች አእምሯዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ ጥበበኛ መሆናችንን እናሳይ። “ንጹሕ አቋም ይዘው የሚመላለሱትን ይሖዋ አንዳች መልካም ነገር” እንደማይነፍጋቸው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 84:11

a ቀኑ ሊቀየር ይችላል።