በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች በባቡር ወደ ሳይቤሪያ የተጋዙበትን ዘመቻ 70ኛ ዓመት ለማስታወስ ሚያዝያ 1, 2021 የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ሚያዝያ 5, 2021
ሩሲያ

ኦፐሬሽን ኖርዝ የተባለውን ዘመቻ 70ኛ ዓመት ለማሰብ በሞስኮ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

ወደ 10,000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሳይቤሪያ ተግዘዋል

ኦፐሬሽን ኖርዝ የተባለውን ዘመቻ 70ኛ ዓመት ለማሰብ በሞስኮ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

ሚያዝያ 1, 2021 ኦፐሬሽን ኖርዝ የተባለውን ዘመቻ 70ኛ ዓመት ለማሰብ በሞስኮ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፤ በ1951 በተካሄደው በዚህ ዘመቻ ወደ 10,000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ውስጥ ከነበሩ ስድስት ሪፑብሊኮች ወደ ሳይቤሪያ በባቡር ተግዘዋል። ምሁራንን እና የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፤ እንዲሁም የጋዜጠኞችን ጥያቄዎች አስተናግደዋል። ስድስቱ ሰዎች ኦፐሬሽን ኖርዝ ስለተባለው ዘመቻ ያብራሩ ከመሆኑም ሌላ በአሁኑ ወቅት በሩሲያ እየደረሰ ያለውን ስደት አያይዘው ጠቅሰዋል። ጋዜጣዊ መግለጫው በኢንተርኔት በቀጥታ ተላልፏል

የአውሮፓ የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ተወካይ የሆነው ያሮስላቭ ሲቩልስኪ ሰብዓዊነት ስለጎደለው ስለዚህ ግዞት ሰፊ መግለጫ ሰጥቷል፤ በግዞት ከተወሰዱት መካከል የያሮስላቭ ሲቩልስኪ ቤተሰብም ይገኙበታል። ያሮስላቭ ሲቩልስኪ እንዲህ ብሏል፦ “የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት በድምሩ 9,793 የይሖዋ ምሥክሮች እና ቤተሰቦቻቸው በግዞት ተወስደዋል። ይህ ቁጥር የሞቱትንና መንገድ ላይ የተወለዱትን ይጨምራል።”

የሩሲያ የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ሰርጌይ ኢቫኔንኮ፣ የሶቪየት መንግሥት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ያናፈሰው ፕሮፓጋንዳ ኦፐሬሽን ኖርዝ እንዲካሄድ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፤ እንዲህ ያለው ፕሮፓጋንዳ በዛሬው ጊዜም በሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት እንዲደርስ እንዳደረገ ገልጸዋል። ሰርጌይ ኢቫኔንኮ ዝርዝር መግለጫ ከሰጡ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ስላሳዩት ጽናት ጎላ አድርገው ተናግረዋል፤ እንዲህ ብለዋል፦ “የሩሲያ ፌዴሬሽን ከ2017 ጀምሮ የይሖዋ ምሥክሮችን ለማፈን እያደረገ ያለው ጥረት ምንም ውጤት አላስገኘም። ኦፐሬሽን ኖርዝ ከተባለው ዘመቻ የተገኘው ትምህርት እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ለእምነታቸው ጥብቅና በመቆም ያሳዩት ጽናት የሩሲያ መንግሥት የሚያደርገው ጥረት ፍሬ ቢስ መሆኑን ያረጋግጣል። ከዚህ አንጻር የሩሲያ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ መብት ለማስከበር እርምጃ ቢወስድ የተሻለ ይሆናል።”

የይሖዋ ምሥክሮች በካዛክስታን፦ ማኅበራዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ዳሰሳ (በ2020 ተሻሽሎ የወጣ) የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ካዛክስታናዊው የሃይማኖት ምሁር አርተር አርቴምዬቭ፣ የሶቪየት መንግሥት የወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ የይሖዋ ምሥክሮችን ማጥፋት ሌላው ቀርቶ ቅንዓታቸውን ማቀዝቀዝ እንኳ እንዳልቻለ ተናግረዋል። እንዲያውም በሶቪየት አገዛዝ ወቅት በካዛክስታን የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር እንደጨመረ እኚህ ምሁር ገልጸዋል። በተመሳሳይም በሞስኮ ሄልሲንኪ ቡድን የሰብዓዊ መብት ባለሙያ የሆኑት ቫለሪ ቦርስቼቭ እንዲህ ብለዋል፦ “ስደት የይሖዋ ምሥክሮችን ይበልጥ ያጠናክራቸዋል እንጂ አያዳክማቸውም። ባለሥልጣናቱ ይህን መገንዘብ አለባቸው።”

በሩሲያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሥር ያለው የምሁራን ምክር ቤት አባል የሆኑት ቫለንቲን ጌፍተር “በዘመናዊቷ ሩሲያ በሕሊናቸው ምክንያት የተፈረደባቸው እስረኞች” በሚል ርዕስ መግለጫ ሰጥተዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ በሩሲያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በሕሊናቸው ምክንያት የተፈረደባቸው እስረኞች እንጂ የፖለቲካ እስረኞች አይደሉም። ቫለንቲን ጌፍተር “የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት ጠላቶች አይደሉም” ብለዋል። አክለውም የይሖዋ ምሥክሮች በሃይማኖታዊ እምነታቸው ምክንያት በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። በመሆኑም ባለሥልጣናቱ የይሖዋ ምሥክሮችን ማሰራቸው አላስፈላጊ እና ፍትሕ የጎደለው እርምጃ ነው።

የመጨረሻውን መግለጫ የሰጡት አሌክሳንደር ቨርኮቭስኪ ናቸው። አሌክሳንደር ቨርኮቭስኪ የፕሬዚዳንቱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል እንዲሁም የሶቫ የመረጃና የጥናት ማዕከል ኃላፊ ናቸው። የሶቫ ማዕከል፣ የፀረ ጽንፈኝነት ሕግ አላግባብ ተግባራዊ የሆነባቸውን ጉዳዮች ያጣራል እንዲሁም ይመዘግባል፤ ማዕከሉ ከሚመለከታቸው ጉዳዮች መካከል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተያያዙ ክሶች ይገኙበታል። አሌክሳንደር ቨርኮቭስኪ በአሁኑ ጊዜ በሩሲያ እየደረሰ ስላለው ስደት ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚደርሰው ስደት ያቆም ይሆን? ይህ በጣም አስፈላጊ ጥያቄ ቢሆንም መልሱን አናውቀውም።” አሌክሳንደር ቨርኮቭስኪ፣ ይዋል ይደር እንጂ የሩሲያ ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚያደርሱትን ስደት ሊያቆሙ እንደሚገባ ገልጸዋል። በተጨማሪም እኚህ ምሁር፣ ሕግ አውጪ አካላት እንደ የይሖዋ ምሥክሮች ያሉ በሰላም እምነታቸውን የሚያራምዱ ሰዎችን መብት በማይጋፋ መልኩ አገሪቱን ከጽንፈኝነት እንቅስቃሴ መጠበቅ እንዲቻል የፀረ ጽንፈኝነት ሕጉን ማስተካከል የሚችሉባቸውን የተለያዩ አማራጮች አቅርበዋል።

የቀረቡትን ንግግሮች በተመለከተ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ለጋዜጠኞች አጋጣሚ ተሰጥቶ ነበር።

በዚሁ ዕለት በቺሲናው፣ ሞልዶቫ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፤ የስብሰባው አዘጋጆች የሞልዶቫ የሳይንስ አካዳሚ የታሪክ ኢንስቲትዩት፣ በባልቲ የሚገኘው የአሌኩ ሩሶ ዩኒቨርሲቲ እና በካሁል የሚገኘው የቦግዳን ፔትሪቼኩ ሃዥዴኡ ዩኒቨርሲቲ ናቸው። ሚያዝያ 9 በዩክሬን ሌላ ስብሰባ ይካሄዳል።