በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ዩሪ ሳቨላየቭ በፍርድ ቤቱ የእስረኞች ማቆያ ክፍል ውስጥ ሆኖ፣ ነሐሴ 26, 2020

ታኅሣሥ 11, 2020
ሩሲያ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ያሳለፈው ወንድም ዩሪ ሳቨላየቭ እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ እስር ሊፈረድበት ይችላል

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ያሳለፈው ወንድም ዩሪ ሳቨላየቭ እስከ ስምንት ዓመት የሚደርስ እስር ሊፈረድበት ይችላል

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

በኖቮስብሪስክ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት በወንድም ዩሪ ሳቨላየቭ ላይ ከተመሠረተው ክስ ጋር በተያያዘ ታኅሣሥ 16, 2020 a ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል። አቃቤ ሕጉ ወንድም ዩሪ የስምንት ዓመት እስር እንዲፈረድበት ጠይቋል። አቃቤ ሕጉ የጠየቀው ፍርድ ከጸና፣ በ2017 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ ካገደበት ጊዜ አንስቶ በወንድሞቻችን ላይ የተላለፈ ረጅሙ የእስር ጊዜ ይሆናል።

አጭር መግለጫ

ዩሪ ሳቨላየቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1954 (ክሮካልዮቭካ፣ ኖቮስብሪስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በልጅነቱ እናቱን በሞት አጥቷል። ያሳደገችው እህቱ ናት። በኃይል ማመንጫ ጣቢያ ውስጥ የቧንቧ ሠራተኛ ሆኖ ይሠራ ነበር። ባለቤቱ ከሞተች በኋላ ለሃይማኖት ትኩረት መስጠት ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄዎቹ አጥጋቢ መልስ እንደሚሰጥ መረዳት ቻለ። በ1996 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ

የክሱ ሂደት

ኅዳር 8, 2018 ፖሊሶች በእሱና በኖቮስብሪስክ ክልል በሚኖሩ ሌሎች ዘጠኝ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ላይ ፍተሻ አደረጉ። ወንድም ዩሪ ችሎት ፊት ሳይቀርብ ታሰረ።

ወንድም ዩሪ በከተማዋ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ አደራጅቷል የሚል ክስ ተመሠረተበት። ከእስር እንዲለቀቅ በተደጋጋሚ ይግባኝ የተጠየቀ ቢሆንም ችሎት ፊት ሳይቀርብ የታሰረበት ወቅት ዘጠኝ ጊዜ እንዲራዘም ተደረገ። በዚህ ሁኔታ ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ቆየ። የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2017 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ካስተላለፈው ውሳኔ ወዲህ ከወንድም ሳቨላየቭ የበለጠ ጊዜ በእስር ያሳለፉት ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰንና ወንድም ሰርጌይ ክሊሞቭ ብቻ ናቸው።

ወንድም ዩሪ ታኅሣሥ 9, 2020 በፍርድ ቤት ፊት የመጨረሻ ንግግሩን ሲያቀርብ ለዳኛው እንዲህ ሲል በድፍረት ተናግሯል፦ “የተከሰስኩት ወንጀል በመሥራቴ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖታዊ ትምህርት በመከተሌ ነው።

“ምንም ጠላት የለኝም፤ ደግሞም በ67 ዓመት የሕይወት ዘመኔ በየትኛውም ወንጀል ተከስሼ አላውቅም። በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ አልገባም። በንግግርም ሆነ በድርጊት የሚፈጸምን ጥቃት እቃወማለሁ፤ በማንም ሰው ላይ ሥነ ልቦናዊ ጫና ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነም አምናለሁ።

“አምላክ የኑሮ ደረጃ፣ ብሔር ወይም ሃይማኖት ሳልለይ ሁሉንም ሰዎች በአክብሮት እንድይዝ እንደሚጠብቅብኝ አውቃለሁ።

“በተጨማሪም የአምላክ ቃል ባለሥልጣናትን እንድናከብር ያበረታታናል። በሮም ላሉ ክርስቲያኖች በተጻፈው ደብዳቤ ላይ ሮም 13:1-3 በከፊል እንዲህ ይላል፦ ‘ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ፤ ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነውና፤ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው። ስለዚህ ባለሥልጣንን የሚቃወም ሁሉ አምላክ ያደረገውን ዝግጅት ይቃወማል።’

“ባለሥልጣናትን አልቃወምም፤ ምክንያቱም አምላክን መቃወም አልፈልግም። አምላክን መቃወም ለሞት የሚዳርግ ከባድ ጥፋት ነው። ስለ እውነተኛው አንድ አምላክና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማወቅ የቻልኩት የይሖዋ ምሥክሮች ስለረዱኝ ነው። ዕድሜ ለእነሱ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ መጽሐፍ እንደሆነ መገንዘብ ችያለሁ። ይህ መጽሐፍ ሁሉንም የሕይወታችንን ክፍሎች ይነካል።”

ወንድም ዩሪ ጠንካራ እምነት ይዞ እንደቀጠለ ማወቃችን ያበረታታናል፤ ይሖዋ ዘላቂ ሰላም በመስጠት እንደባረከው በግልጽ ማየት ይቻላል።—ኢሳይያስ 26:3

a ቀኑ ሊቀየር ይችላል።