በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሩሲያ ውስጥ የገደብ እስራት ከተበየነባቸው ከ80 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች መካከል ሦስቱ

ጥቅምት 14, 2021
ሩሲያ

ከ80 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የገደብ እስራት ተፈርዶባቸዋል—ሕይወታቸው ምን ይመስላል?

ከ80 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የገደብ እስራት ተፈርዶባቸዋል—ሕይወታቸው ምን ይመስላል?

ሚያዝያ 2017 ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ላይ እገዳ ከጣለች ወዲህ ከ500 በላይ ወንድሞችና እህቶች በቁጥጥር ሥር ውለው በጽንፈኝነት ወንጀል ተከስሰዋል። ወደ 40 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች እስራት የተፈረደባቸው ሲሆን 15 የሚሆኑት ደግሞ የገንዘብ መቀጮ ተጥሎባቸዋል። ከ80 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብለው የገደብ እስራት ተበይኖባቸዋል። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች እስር ቤት ባይገቡም የተላለፈባቸው የገደብ እስራት ጨርሶ ፍትሐዊ አይደለም፤ ያስከተለባቸው ብዙ ጉዳቶችም አሉ።

በሩሲያ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት አንድ ዳኛ በእስራት ፋንታ የገደብ እስራት ብይን የማስተላለፍ ሥልጣን አለው። እንዲህ ዓይነት ብይን ከተላለፈ ዳኛው ግለሰቡ በክትትል የሚቆይበትን ጊዜ ይወስናል እንዲሁም አንዳንድ እገዳዎች ወይም ክልከላዎች ይጥላል። ግለሰቡ የተጣለበትን እገዳ ከጣሰ ፍርድ ቤቱ የገደብ እስራቱን ወደ እስራት ሊቀይረው ይችላል።

የገደብ እስራት የተፈረደባቸው ሰዎች ሕይወት ምን ይመስላል? ይሖዋ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እየረዳቸው ያለው እንዴት ነው? ከሁለት እስከ ስድስት ዓመት የሚደርስ የገደብ እስራት ለተጣለባቸው አንዳንድ ወንድሞች ቃለ መጠይቅ አድርገናል። እነዚህ ወንድሞች ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎችና ይሖዋ እንዴት እንደረዳቸው ተናግረዋል።

የገደብ እስራት የተበየነባቸው ወንድሞች ሕይወት ምን እንደሚመስል ማወቃችን ስለ እነሱና ስለ ቤተሰቦቻቸው ይበልጥ እንድንጸልይ ያነሳሳናል። የእነሱ ተሞክሮ እንደሚያረጋግጠው ይሖዋ እንዲህ ላሉ ጸሎቶች መልስ ይሰጣል፤ እንዲሁም ታማኝ አገልጋዮቹን በሚደርስባቸው መከራ ሁሉ ይደግፋቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4