በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሮማን ባራኖቭስኪ እና እናቱ እህት ቫለንቲና ባራኖቭስካያ

ጥር 29, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ | ሩሲያ ውስጥ ወንድም ሮማን ባራኖቭስኪ እና እናቱ እህት ቫለንቲና ባራኖቭስካያ ጥፋተኛ ተብለው ሊፈረድባቸው ይችላል

ወቅታዊ መረጃ | ሩሲያ ውስጥ ወንድም ሮማን ባራኖቭስኪ እና እናቱ እህት ቫለንቲና ባራኖቭስካያ ጥፋተኛ ተብለው ሊፈረድባቸው ይችላል

ግንቦት 4, 2022 በካካሲያ የሚገኘው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የ71 ዓመቷ እህት ቫለንቲና ባራኖቭስካያ ከእስር እንድትለቀቅ ወሰነ። ፍርድ ቤቱ፣ አቃቤ ሕጉ እህት ቫለንቲና ከእስር እንዳትለቀቅ ለማድረግ ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ አድርጓል። እህት ቫለንቲና ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ቆይታለች። ልጇ ሮማን አሁንም በእምነቱ ምክንያት እንደታሰረ ነው።

መጋቢት 4, 2022 የኡስት አባካን አውራጃ ፍርድ ቤት ቫለንቲና በአመክሮ እንድትፈታ ያደረገውን ውሳኔ የአቃቤ ሕጉ ቢሮ ይግባኝ አለ። አቃቤ ሕጉ ቫለንቲና “ለወንጀሏ ይቅርታ ስላልጠየቀች” የእስር ጊዜዋን ሳትጨርስ መለቀቅ እንደሌለባት ተከራክሯል። ቫለንቲና ቢያንስ የአቃቤ ሕጉ ይግባኝ እስኪሰማ ድረስ እስር ቤት ትቆያለች።

ግንቦት 24, 2021 በሩሲያ የሚገኘው የካካሲያ ሪፑብሊክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንድም ሮማን ባራኖቭስኪ እና የ70 ዓመቷ እናቱ ቫለንቲና ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። ሁለቱም እንደታሰሩ ይቆያሉ። ወደፊት ከእስር ከተለቀቁ በኋላም ተጨማሪ ገደቦች እንደሚጣሉባቸው ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

የካቲት 24, 2021 በካካሲያ ሪፑብሊክ የሚገኘው የአባካን ከተማ ፍርድ ቤት በሮማን ላይ የስድስት ዓመት እስራት በየነበት። ፍርድ ቤቱ በሮማን እናት በቫለንቲና ላይም የሁለት ዓመት እስራት በይኗል። በሩሲያ ውስጥ አንዲት እህት በእምነቷ የተነሳ እስር ሲፈረድባት ይህ የመጀመሪያው ነው። ቫለንቲና ሚያዝያ 2021 ላይ 70 ዓመት ይሞላታል፤ ሐምሌ 2020 ደግሞ በስትሮክ ተመትታ ነበር። ብይኑ እንደተላለፈ ሁለቱም ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።

አጭር መግለጫ

ሮማን ባራኖቭስኪ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1974 (ባላኮቮ፣ ሳራቶቭ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ቤቶች በማደስ ሙያ ላይ ተሰማርቶ ራሱንና እናቱን ያስተዳድራል። ጊታር፣ ቼዝና እግር ኳስ መጫወት ይወዳል

    በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ የሕይወት ዓላማ ያሳስበው ነበር። “አንዳንድ ጊዜ፣ አምላክ የሕይወትን መንገድ እንዲያሳየኝ እለምነው ነበር” ብሏል። በ1993 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረ። በ1997 ተጠመቀ

ቫለንቲና ባራኖቭስካያ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1951 (ቫኖቭካ፣ ካዛክስታን)

  • ግለ ታሪክ፦ በ2006 ጡረታ እስከወጣችበት ጊዜ ድረስ የሒሳብ ባለሙያ እና የፋይናንስ አማካሪ ሆና ትሠራ ነበር። ምግብ ማብሰል እንዲሁም ሙዚቃና ግጥም መጻፍ ትወዳለች

    በ1995 እሷም እንደ ልጇ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። በተለይ ልቧን የነካው አምላክ እንደማይዋሽ ማወቋ ነው። በ1996 ተጠመቀች

የክሱ ሂደት

ሚያዝያ 10, 2019 ምሽት ላይ የአባካን ከተማ ፖሊሶች የወንድም ሮማን ባራኖቭስኪን እና የእናቱን የቫለንቲናን ቤት ጨምሮ አራት ቤቶችን በረበሩ። ፖሊሶቹ መጽሐፍ ቅዱሶቻቸውን፣ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻቸውንና የግል ሰነዶቻቸውን ወረሱባቸው። ከዚያም በሮማን እና በቫለንቲና ላይ የወንጀል ክስ ተመሠረተ።

ሮማን እንዲህ ብሏል፦ “ቤታችን በተበረበረበት ወቅት በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ 1 ቆሮንቶስ 10:13⁠ን ተወያይተን መጨረሳችን ነበር። ጥቅሱ ጠቃሚ ሐሳብ ይዟል፤ ይሖዋ የሚደርስብንን ፈተና አይመርጥልንም። . . . ይሖዋ ‘አንተ ጠንካራ ስለሆንክ ይህን ፈተና ትችለዋለህ፤ አንተ ደግሞ ደካማ ስለሆንክ ቀለል ያለ ፈተና ይገጥምሃል’ አይልም። እንዲህ የሚያደርግ ቢሆን ኖሮ ሁሉም ነገር በእኛ አቅም ላይ የተመካ ይሆን ነበር። ማናችንም የተለያየ ፈተና ሊያጋጥመን ይችላል። ይሖዋ በሚሰጠን ኃይል ከታመንን ሁላችንም ፈተናውን በጽናት መወጣት እንችላለን።”

ሐምሌ 2020 ቫለንቲና አንጎሏ ውስጥ ደም ፈሰሰ። እንዲህ ብላለች፦ “የጤናዬ ሁኔታ እየተባባሰ በሄደ መጠን ይሖዋ ከጎኔ እንደሆነ ይበልጥ በግልጽ ይታየኝ ነበር። ይህ የሆነው መጸለዬን ስላላቋረጥኩ ነው፤ ይሖዋ እቅፍ ያደረገኝ ያህል ሆኖ ይሰማኝ ነበር። የነበረኝን ሰላምና መረጋጋት በቃላት መግለጽ ይከብደኛል።”

ቫለንቲና ያጋጠሟት ነገሮች የሚከተለው መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ አድርገዋታል፦ “አባታችንን ለዘላለም ለማገልገልና ምንም ነገር ቢያጋጥመኝ ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ።”

ሮማን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ እንዲሁም በዘመናችን ባሉ የጽናት ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰሉ እምነቱን እንዳጠናከረለት ተናግሯል። እንዲህ ባሉት ምሳሌዎች ላይ ሲያሰላስል ብዙውን ጊዜ ራሱን እንዲህ በማለት ይጠይቃል፦ ‘ምን ዓይነት ፈተና አጋጥሟቸዋል? ፈተና የደረሰባቸው ለምንድን ነው? ታማኝነታቸውን ለመጠበቅ የረዳቸው ምንድን ነው? ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት የደገፋቸው እንዴት ነው?’ ሮማን ለእነዚህ ጥያቄዎች ያገኘው መልስ “ይሖዋ አስፈላጊ ከሆነ ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል” እንደሚሰጠው ይበልጥ እንዲተማመን አድርጎታል።

ሮማን፣ ቫለንቲና እንዲሁም በሩሲያ የሚገኙ ውድ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በሙሉ ይሖዋን መጠጊያቸውና ብርታታቸው አድርገው ማየታቸውን እንዲቀጥሉ እንጸልያለን።—መዝሙር 46:1