በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ኢልሃም ካሪሞቭ፣ ወንድም ኮንስታንቲን ማትራሾቭ፣ ወንድም ቭላዲሚር ምያኩሻይን እና ወንድም አይዳር ዩልሜትዬቭ

ግንቦት 19, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ | በታታርስታን የሚኖሩ ወንድሞች ክስ በተመሠረተባቸው ወቅት የይሖዋ ድጋፍ ስላልተለያቸው አመስጋኝ ናቸው

ወቅታዊ መረጃ | በታታርስታን የሚኖሩ ወንድሞች ክስ በተመሠረተባቸው ወቅት የይሖዋ ድጋፍ ስላልተለያቸው አመስጋኝ ናቸው

መስከረም 2, 2022 የታታርስታን ሪፑብሊክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንድም ኢልሃም ካሪሞቭ፣ ወንድም ኮንስታንቲን ማትራሾቭ፣ ወንድም ቭላዲሚር ምያኩሻይን እና ወንድም አይዳር ዩልሜትዬቭ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል። እርግጥ በአሁኑ ወቅት ወህኒ አይወርዱም።

ታኅሣሥ 16, 2021 የታታርስታን ሪፑብሊክ የናቤሬዥንዬ ቼልኒ ከተማ ፍርድ ቤት ኢልሃም፣ ኮንስታንቲን፣ ቭላዲሚር እና አይዳር ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላልፏል። ኢልሃም እና ኮንስታንቲን የሁለት ዓመት ከስድስት ወር የገደብ እስራት ተበይኖባቸዋል። ቭላዲሚር የሦስት ዓመት ከአንድ ወር፣ አይዳር ደግሞ የሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር የገደብ እስራት ተበይኖባቸዋል።

አጭር መግለጫ

ኢልሃም ካሪሞቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1981 (ዠምባይ፣ ኡዝቤኪስታን)

  • ግለ ታሪክ፦ የጠርሙስ ሥራ ባለሙያ ነው። ኡዝቤኪስታን እያለ ቤተሰቡን ለማስተዳደር የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራ ነበር። በ2000 ወደ ሩሲያ ሄዶ በዚያ መኖር ጀመረ። በ2001 አንድ ቀን አምላክ እንዲረዳው ጸለየ። በቀጣዩ ቀን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ2004 ተጠመቀ። በ2012 ከዩልያ ጋር ትዳር መሠረተ

ኮንስታንቲን ማትራሾቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1988 (ፕረኮፕየፍስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ አባቱ የሞቱት ትንሽ ልጅ እያለ ነው። ሜካኒክ ነው። እናቱን የሚያስተዳድረው እሱ ነው፤ እናቱ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ ማረከው። በ2018 ተጠመቀ

ቭላዲሚር ምያኩሻይን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1987 (ኒዥንየካምስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ከቴክኒክ ኮሌጅ እና ከምሕንድስና ትምህርት ቤት ተመርቋል። የተሽከርካሪ የኤሌክትሪክ ቁሳቁስ በሚሠራ ድርጅት ውስጥ ዋና መሐንዲስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ ያዘለ፣ ግልጽ እንዲሁም ምክንያታዊ መሆኑ አስደነቀው። በ2013 ተጠመቀ። በ2017 ከስቬትላና ጋር ትዳር መሠረተ

አይዳር ዩልሜትዬቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1993 (ኒዥንየካምስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ የሙዚቃና የመኪና ሜካኒክነት ሥልጠና ወስዷል። በሽያጭ ሙያ እና በሜካኒክነት ይሠራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ወላጆቹን የጠቀማቸው እንዴት እንደሆነ ካየ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ2012 ተጠመቀ። በ2013 ከአልቢና ጋር ትዳር መሠረተ። በመጽሐፍ ቅዱስ በሠለጠነ ሕሊናው የተነሳ በውትድርና አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ አልሆነም። በምትኩ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ሰጥቷል

የክሱ ሂደት

ግንቦት 27, 2018 የታታርስታን የደህንነት ፖሊሶች የአሥር የይሖዋ ምሥክሮችን ቤት ከፈተሹ በኋላ ኢልሃምን፣ ኮንስታንቲንን፣ ቭላዲሚርን እና አይዳርን ማረፊያ ቤት አስገቧቸው። አራቱም በማረፊያ ቤት ከ160 ቀን በላይ ከቆዩ በኋላ የቁም እስረኛ እንዲሆኑ ተደረገ።

በአሁኑ ወቅት ከቁም እስር የተፈቱ ቢሆንም አራቱም በሩሲያ መንግሥት “የጽንፈኞች” ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፤ እንዲሁም ከአካባቢው እንዳይወጡ ፍርድ ቤት እገዳ ጥሎባቸዋል። በመሆኑም የባንክ ሒሳባቸውን ማንቀሳቀስ አይችሉም፤ ሥራ ማግኘትም ከባድ ሆኖባቸዋል።

አይዳር ማረፊያ ቤት ስለነበረበት ጊዜ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ጥቅሶችን አስታወስኩ። . . . በራሴ ቢሆን ማስታወስ የማልችላቸውን ብዙ ሐሳቦች እንዳስታውስ ይሖዋ ረድቶኛል።”

ኮንስታንቲን ማረፊያ ቤት እንደገባ ፈርቶ ነበር። ሆኖም ወዲያውኑ ለፍርድ ቤቱ ባለሥልጣናት፣ ለጠባቂዎቹ፣ ለሌሎቹ እስረኞች፣ ለፖሊሶቹና ለማረፊያ ቤቱ ኃላፊዎች ለመስበክ ጥረት ማድረግ ጀመረ። እንዲህ ብሏል፦ “ማረፊያ ቤት መግባቴ ነፃ ከነበርኩበት ጊዜ የበለጠ ምሥክርነት መስጠት እንድችል ረድቶኛል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በፊልጵስዩስ 1:12, 13 ላይ የጻፈው ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞኛል፦ ‘እንግዲህ ወንድሞች፣ እኔ ያጋጠመኝ ሁኔታ ምሥራቹ ይበልጥ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እንዳደረገ እንድታውቁ እወዳለሁ፤ የታሰርኩት የክርስቶስ አገልጋይ በመሆኔ የተነሳ እንደሆነ በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ሁሉና በሌሎች ሰዎች ሁሉ ዘንድ በይፋ ታውቋል።’”

ቭላዲሚር ወንድሞችና እህቶች ላበረከቱለት እርዳታ አድናቆቱን ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞችና እህቶች አንዳንድ ቁሳቁሶችን ገዝታ እንድትልክልኝ በተደጋጋሚ ገንዘብ እንደሰጧት ባለቤቴ ነግራኛለች። ማረፊያ ቤቱ በወር ውስጥ በሚገባልን ቁሳቁስ መጠን ላይ ገደብ ጥሏል፤ በአብዛኛው የተፈቀደው ገደብ ላይ እስኪደርስ ድረስ ብዙ ነገር ይላክልኝ ነበር።”

ኢልሃም ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና እንደተጠናከረ ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ፈተና ወደ ሰማዩ አባቴ ይበልጥ እንድቀርብ ረድቶኛል። አሁን በእሱ ይበልጥ እተማመናለሁ፤ እንዲሁም ከበፊቱ ይበልጥ የእሱን እርዳታ እጠይቃለሁ። ለይሖዋ የማቀርበው ጸሎት ይበልጥ ረጅም፣ ጥልቀት ያለውና ልባዊ ሆኗል።”

እነዚህ ወንድሞችና ቤተሰቦቻቸው በዚህ የመከራ ወቅት ‘ለአምላክ በማደራቸውና ሁሉንም ነገር በትጋት በማከናወናቸው’ እንደሚባረኩ እርግጠኞች ነን።—1 ጢሞቴዎስ 2:2

ፍርድ ቤቱ ብይን የሚያስተላልፍበትን ቀን አስቀድሞ የማያሳውቅበት ጊዜ አለ።