በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የላይኛው መደዳ (ከግራ ወደ ቀኝ)፦ ወንድም ቦሪስ ቡሪሎቭ፣ ወንድም አሌክሳንደር ኢኖዜምትሴቭ

የታችኛው መደዳ (ከግራ ወደ ቀኝ)፦ ወንድም ቪክቶር ኩችኮቭ፣ ወንድም ኢጎር ቱሪክ እና ወንድም ዩሪ ቫግ

ሚያዝያ 21, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ | ቤታቸው የተፈተሸባቸውና ለእስር የተዳረጉ በፐርም፣ ሩሲያ ያሉ አምስት ወንድሞች ደፋርና ደስተኛ ሆነው ቀጥለዋል

ወቅታዊ መረጃ | ቤታቸው የተፈተሸባቸውና ለእስር የተዳረጉ በፐርም፣ ሩሲያ ያሉ አምስት ወንድሞች ደፋርና ደስተኛ ሆነው ቀጥለዋል

ግንቦት 12, 2022 ሰባተኛው ጠቅላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ወንድም ቦሪስ ቡሪሎቭ፣ ወንድም አሌክሳንደር ኢኖዜምትሴቭ፣ ወንድም ቪክቶር ኩችኮቭ፣ ወንድም ኢጎር ቱሪክ እና ወንድም ዩሪ ቫግ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። እርግጥ ወንድሞች አሁን ወህኒ አይወርዱም።

ነሐሴ 23, 2021 የፐርም ክልላዊ ፍርድ ቤት ቦሪስ፣ አሌክሳንደር፣ ቪክቶር፣ ኢጎር እና ዩሪ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። መጀመሪያ ላይ የተላለፈባቸው ብይን በዚያው ይጸናል።

ግንቦት 12, 2021 የፐርም ከተማ ኢንደስትሪያል አውራጃ ፍርድ ቤት ቦሪስ፣ አሌክሳንደር፣ ቪክቶር፣ ኢጎር፣ እና ዩሪ የተባሉ ወንድሞችን ጉዳይ ተመልክቶ ውሳኔ አስተላልፏል። ኢጎር የሰባት ዓመት የገደብ እስር ተፈርዶበታል። ቀሪዎቹ አራት ወንድሞች ደግሞ በሁለት ዓመት ተኩል የገደብ እስር እንዲቀጡ ተወስኗል።

አጭር መግለጫ

ቦሪስ ቡሪሎቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1941 (ሴቫስቶፖል)

  • ግለ ታሪክ፦ ያደገው በፐርም ክልል ነው። በሰብል ምርትና በአፈር አያያዝ ጥናት ዲግሪ አለው። ልጅ ሳለ እናቱ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ታነብለት ነበር። በ1990ዎቹ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አገኘ። በ1996 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ

አሌክሳንደር ኢኖዜምትሴቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1972 (ኮስታናይ)

  • ግለ ታሪክ፦ በውትድርና አገልግሏል። ቀደም ሲል የኤሌክትሪክ ባለሙያና መካኒክ ሆኖ ሠርቷል፤ በአሁኑ ጊዜ በሕንፃ ጥገናና አፓርታማዎችን በማደስ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ከጀመረ በኋላ በሰዎች ላይ ኢፍትሐዊ ነገር የሚደርስበትንና የሚሞቱበትን ምክንያት በተመለከተ አጥጋቢ መልስ አገኘ። በ1996 ተጠመቀ። በ2017 ከባለቤቱ ከኦሌስያ ጋር ትዳር መሠረተ። አንድ ላይ ሆነው የባለቤቱን ሴት ልጅ እያሳደጉ ነው። ሥዕል መሣል፣ ሆኪ መጫወትና ዓሣ ማጥመድ ያስደስተዋል

ቪክቶር ኩችኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1967 (ስቬትሊትሳ)

  • ግለ ታሪክ፦ ከልጅነቱ አንስቶ የእንጨት ቅርጻ ቅርጾችን መሥራት ያስደስተው ነበር። በብረት ምሕንድስና ሥልጠና ያገኘ ሲሆን የንድፍ መሐንዲስ ሆኖ ሠርቷል። ዓሣ ማጥመድና መረብ ኳስ መጫወት ይወዳል። በ1988 ከባለቤቱ ከታንያ ጋር ትዳር መሠረተ። አንዲት ሴት ልጅ አላቸው። ከድሮ ጀምሮ ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች መወያየት ያስደስተዋል። በ1993 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ

ኢጎር ቱሪክ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1968 (ኔሊዶቮ)

  • ግለ ታሪክ፦ ፎቶ አንሺና የሥነ ሕንፃ ባለሙያ ሆኖ ይሠራል። በ1990ዎቹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑ አስገረመው። በ1998 ተጠመቀ። በ2002 ትዳር የመሠረተ ሲሆን የአንድ ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነው። በትርፍ ጊዜው ፎቶ ማንሳት፣ ቪዲዮ መቅረጽና ከሬዲዮ ጋር የተያያዙ ነገሮችን መሥራት ያስደስተዋል

ዩሪ ቫግ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1975 (ሌሶሲቢርስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ የከባድ ዕቃ ማንሻ ክሬን በማንቀሳቀስ ሙያ ሥልጠና አግኝቷል። አሁን በኤሌክትሪክና በሕንፃ ጥገና ሙያ ተሰማርቷል። ወታደር ሳለ እህቱ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ነገረችው። እህቱ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ በማድረጓ ያገኘችውን ጥቅም ማየቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት አነሳሳው። በ1996 ተጠመቀ። በዚያው ዓመት ከሚስቱ ከስቬትላና ጋር ትዳር መሠረተ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አላቸው

የክሱ ሂደት

መስከረም 17, 2018 የፌዴራል ደህንነት አገልግሎትና ሌሎች ልዩ ኃይሎች በፐርም ክልል የፍተሻ ዘመቻ አካሄዱ። ቢያንስ አሥር የሚያህሉ የወንድሞቻችን ቤቶች ፍተሻ ተካሂዶባቸዋል። ፖሊሶቹ በፍተሻው ወቅት ያገኙትን ገንዘብ፣ ሞባይል ስልክና ሌሎች ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ወሰዱ። ቪክቶር እና ኢጎር ለበርካታ ቀናት ከታሰሩ በኋላ አራት ወር ለሚጠጋ ጊዜ በቁም እስር እንዲቆዩ ተደርገዋል። አሁን ሁሉም በተፈለጉ ሰዓት ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ የሚገልጽ ስምምነት ፈርመዋል። ስማቸው በሩሲያ “ጽንፈኞች” ዝርዝር ውስጥ ገብቷል።

እነዚህ ወንድሞች ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ሁሉም አስደናቂ ድፍረት እያሳዩ ነው፤ ደግሞም ደስታቸውን ጠብቀው ቀጥለዋል።

ዩሪ አሁን ከድሮው የበለጠ ወደ ይሖዋ አዘውትሮ እንደሚጸልይ ተናግሯል። በተጨማሪም ይሖዋ እሱን እንዴት እየደገፈውና እያበረታታው እንዳለ በተደጋጋሚ ያሰላስላል። እንዲህ ብሏል፦ “በኢያሱ 1:7 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እንድረጋጋ ይረዳኛል። ይህ ጥቅስ ተግባር ላይ ላውለው የሚገባ ጥሩ መመሪያ ሰጥቶኛል። ይሖዋ እየረዳኝና እየተንከባከበኝ እንዳለ ማስተዋል ችያለሁ።”

ቪክቶር ስለ ይሖዋ ድርጅት ማሰላሰሉ በክስ ሂደቱ ወቅት እንዲረጋጋ እንደረዳው አስተውሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ይሖዋ ታላቅነት፣ በዓይን ስለሚታየውም ሆነ ስለማይታየው የድርጅቱ ክፍል፣ ልዩ ስለሆነው የወንድማማች ማኅበራችን፣ ስለ ስብከቱ ሥራ ስፋት እንዲሁም እውነት ስላለው ውድ ዋጋ ለማሰላሰል እሞክር ነበር። እንዲህ ማድረጌ በራሴ ላይ እንዳላተኩር ረድቶኛል። ሁሉንም ነገር በተረጋጋ መንፈስ እንዳይ አስችሎኛል።”

ኢጎር፣ ወደ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ ቀደም ሲል ስላሳለፋቸው አንዳንድ ነገሮች ሲያስብ ፈገግ እንደሚል ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ማረፊያ ቤት ሳለሁ ልጄ እኔን ለማበረታታት የአዲሱን ዓለም ሥዕል ሣለችልኝ። የማረፊያ ቤቱ ጠባቂዎች ግን ሥዕሉን ለእኔ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ባለቤቴ፣ ጠባቂዎቹ ሥዕሉን ለረጅም ሰዓት ካዩት በኋላ ‘ይሄን ልንሰጠው አንችልም። ስናየው ከእስር ቤት ለማምለጥ የሚረዳ ንድፍ ይመስላል’ በማለት መልሰው እንደሰጧት ነገረችኝ።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “እርግጥ አልተሳሳቱም፤ ከዚህ ክፉ ሥርዓት ‘ልናመልጥ’ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ አዲሱ ዓለም ነው!”

ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እነዚህን ወንድሞችና ቤተሰቦቻቸውን መደገፉን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን። ይሖዋ ምንጊዜም የሚያስፈልጋቸውን ብርታት እንደሚሰጣቸው እንተማመናለን።—ኤፌሶን 3:20