በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ቪክተር ሺፒሎቭ (ጠበቃ)፣ ወንድም ኮንስታንቲን ባዠኖቭ፣ እህት ስኔዣና ባዠኖቫ፣ እህት ቬራ ዞሎቶቫ፣ ቪክተር ዤንኮቭ (ጠበቃ) እና ማክሲም ኖቫኮቭ (ጠበቃ)

ኅዳር 17, 2020 | የታደሰው፦ የካቲት 1, 2023
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ—አዲስ ብይን ተላለፈ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ያቀረቡትን የይግባኝ ጥያቄ ውድቅ አደረገ

ወቅታዊ መረጃ—አዲስ ብይን ተላለፈ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ያቀረቡትን የይግባኝ ጥያቄ ውድቅ አደረገ

ጥር 31, 2023 የካምቻትካ ክልል ፍርድ ቤት ኮንስታንቲን፣ ባለቤቱ ስኔዣና እና ቬራ ቀደም ሲል የተላለፈባቸው የሁለት ዓመት የገደብ እስራት ተፈጻሚ እንዲሆን ወስኗል። በአሁኑ ወቅት ወህኒ አይወርዱም።

ታኅሣሥ 15, 2022 የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል ነክ ጉዳዮች የዳኝነት ቦርድ፣ ወንድም ኮንስታንቲን ባዠኖቭ፣ ባለቤቱ ስኔዣና እና እህት ቬራ ዞሎቶቫ ከተመሠረቱባቸው ክሶች በሙሉ ነፃ እንዲሆኑ የተላለፈውን ብይን ሽሮታል። በመሆኑም ጉዳያቸው ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ተመልሷል። የፍርድ ሂደቱ በተከናወነበት ወቅት ቢያንስ የስድስት ኤምባሲዎች ተወካዮች ለይሖዋ ምሥክሮች ድጋፋቸውን ለማሳየት በቦታው ተገኝተው ነበር።

ኮንስታንቲን፣ ስኔዣና እና ቬራ ከተመሠረቱባቸው ክሶች በሙሉ ነፃ እንዲሆኑ የተላለፈው ብይን እንዲሻር አቃቤ ሕጉ ለዘጠነኛው ጠቅላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ነበር፤ ፍርድ ቤቱ ግን ሰኔ 10, 2022 የአቃቤ ሕጉን ጥያቄ ውድቅ አደረገው። በመሆኑም አቃቤ ሕጉ ለሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አለ።

ጥር 18, 2022 የካምቻትካ ክልል ፍርድ ቤት ኮንስታንቲን፣ ባለቤቱ ስኔዣና እና ቬራ ያቀረቡትን ሁለተኛ የይግባኝ ጥያቄ ተቀበለ። ከተመሠረቱባቸው ክሶች በሙሉ ነፃ ተደርገዋል፤ ይህ ውሳኔ ወዲያውኑ ተግባራዊ ሆኗል። ሦስቱም የይሖዋ ምሥክሮች ለተላለፈባቸው ተገቢ ያልሆነ ፍርድ ካሳ መጠየቅ ይችላሉ። አቃቤ ሕጉ ይግባኝ ይጠይቃል።

ኅዳር 17, 2020 የካምቻትካ ክልል ፍርድ ቤት ኮንስታንቲን፣ ባለቤቱ ስኔዣና እና ቬራ ያቀረቡትን የይግባኝ ጥያቄ ውድቅ አደረገ። በመሆኑም ቀደም ሲል የተላለፈባቸው የሁለት ዓመት የገደብ እስራት ፍርድ ተፈጻሚ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት ሦስቱም እስር ቤት የማይገቡ ሲሆን ደስታቸውን ጠብቀው በጽናት ቀጥለዋል።

መስከረም 25, 2020 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ክሱ በተሰማበት ዕለት ወንድም ባዠኖቭ፣ የሚተላለፍበት ፍርድ እንደማያስፈራው በድፍረት ተናግሮ ነበር። እንዲሁም በዮሐንስ 15:20 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ስደት እንደሚደርስባቸው የተናገረው ሐሳብ በእሱ ላይ እየተፈጸመ በመሆኑ ክብር እንደሚሰማው ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ወንድም ባዠኖቭ፣ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲሰብኩ እንዳዘዛቸው ተናግሯል። ከዚያም የሚከተለውን ከባድ ጥያቄ አቅርቧል፦ “ክርስቶስ ያዘዘውን ነገር የመሻር ወይም የመከልከል መብት ያለው ማን ነው?” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ዝም ልል አልችልም። . . . በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች ለሰዎች መናገሬን እቀጥላለሁ።”