በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ስቬትላና ሞኒስ ከባለቤቷ ከአላም አሊዬቭ ጋር

የካቲት 3, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ—እህት ተፈረደባት | እህት ስቬትላና ሞኒስ በእምነቷ ምክንያት ሊፈረድባት ቢችልም አዎንታዊ አመለካከት አላት

ወቅታዊ መረጃ—እህት ተፈረደባት | እህት ስቬትላና ሞኒስ በእምነቷ ምክንያት ሊፈረድባት ቢችልም አዎንታዊ አመለካከት አላት

ጥቅምት 31, 2022 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት በእህት ስቬትላና ሞኒስ ላይ የጥፋተኛነት ብይን አስተላልፏል፤ የሁለት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት በይኖባታል። አሁን እስር ቤት አትገባም።

መጋቢት 9, 2022 የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል ፍርድ ቤት የስቬትላናን የጥፋተኛነት ብይን ሽሯል። ክሷ እንደገና እንዲታይ በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል ወደሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት ተመልሷል።

የካቲት 15, 2021 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት፣ ስቬትላና በታገደ ድርጅት እንቅስቃሴ ተካፍላለች የሚል የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ 10,000 ሩብል (135 የአሜሪካ ዶላር) የገንዘብ መቀጮ እንድትከፍል ወስኗል።

አጭር መግለጫ

ስቬትላና ሞኒስ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1977 (ሌሶዛቮድስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ እየተባባሰ የሚሄድ የዓይን ሕመም አለባት። ቋንቋ መማር ትወዳለች። ቻይንኛ፣ እንግሊዝኛና ጀርመንኛ ተምራለች። ለዓመታት ልጇን ያሳደገችው ብቻዋን ነው። አነስተኛ የቻይና ምግብ ቤት ከፍታ ቤተሰቧን ታስተዳድር ነበር

    በዓለም ላይ ያለው ግፍ በጣም ስለረበሻት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። በ2005 ተጠመቀች። በ2015 ከአላም አሊዬቭ ጋር ትዳር መሠረተች፤ እሱም ለብቻው ክስ ተመሥርቶበታል

የክሱ ሂደት

በፌዴራል ደህንነት ቢሮ ዋና መርማሪ የሆነው ሌተና ያንኪን፣ መስከረም 26, 2019 በእህት ስቬትላና ሞኒስ ላይ የወንጀል ክስ መሠረተ። ስቬትላና የ91 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን አያቷን ለመርዳት መኪና መጠቀም ቢያስፈልጋትም ፍርድ ቤቱ ወደ ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ መኪናዋን እንዳትጠቀም አግዷት ነበር።

የመጀመሪያው ምርመራ ያበቃው ታኅሣሥ 2019 ነው። ከዚያም ባለሥልጣናቱ ክሱን ወደ ቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት መሩት።

ስቬትላና ስለደረሰባት ስደት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ቤታችን በተበረበረበት ወቅት ተረጋግቼ ነበር። ‘ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው’ የሚለውን ጥቅስ እውነተኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተረዳሁት በዚያ ወቅት ነው።”—ማቴዎስ 5:10

ከፍተሻው በኋላ የስቬትላና ባለቤት አላምም በቁጥጥር ሥር ውሎ ለስምንት ቀን ያህል ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደርጎ ነበር። ስቬትላና እንዲህ ብላለች፦ “ስለ እሱ ከልክ በላይ መጨነቄን ማቆም በጣም ከብዶኝ ነበር። ሁኔታው ያሳሰበኝ ባለቤቴ የነበረበት ከባድ የወገብ ሕመም ተባብሶ ስለነበረ ነው፤ ፍተሻው ከመካሄዱ ከአንድ ሳምንት በፊት ሆስፒታል ሄዶ መታከም አስፈልጎት ነበር። አላምን ማግኘት የምችልበት ምንም መንገድ ስላልነበረ ደህንነቱን ማረጋገጥ አልቻልኩም። ስሜቴን አውጥቼ ለይሖዋ ነገርኩት፤ የሚያሳስበኝን ነገር ሁሉ በእሱ እጅ እንደጣልኩት እና አላምን ከማንም በተሻለ እንደሚንከባከብልኝ እንደምተማመን ገለጽኩለት።”

ስቬትላና ይሖዋ ከጎኗ እንዳለ ጨርሶ ተጠራጥራ አታውቅም። እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋን እርዳታ በሕይወቴ ተመልክቻለሁ። ወቅቱ በፍርሃት የምንርድበት ጊዜ እንዳልሆነ ገብቶኝ ነበር። . . . በራሴ ላይ ላለማተኮር ጥረት አደረግኩ። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ታማኝ መሆን በምችልበት መንገድ ላይ አተኮርኩ።”

ስቬትላና እና አላም አዎንታዊ አመለካከት ይዘው ለመቀጠል ሲሉ እምነታቸውን ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። ስቬትላና እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ በየቀኑ የዕለቱን ጥቅስ እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ምዕራፍ አንብበን እንወያይበታለን። በተለይ ከይሖዋ መጽናኛ እንድናገኝና በእሱ እንድንታመን በሚያበረታቱ ጥቅሶች ላይ ትኩረት እናደርጋለን።” በኢሳይያስ 41:10 ላይ የሚገኘው “እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ” የሚለው የ2019 የዓመት ጥቅስ ስቬትላናን እና አላምን ይሖዋ እንደሚወዳቸው ምንጊዜም እንዲያስታውሱ ይረዳቸዋል። ስቬትላና “ይህን ጥቅስ አሳትመን በፍሬም አስቀምጠነዋል” ብላለች።

የስቬትላና ጽናት የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ቤተሰቦቿ አመለካከታቸውን እንዲቀይሩ አድርጓቸዋል። ስቬትላና እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ቀደም ሲል ተቃዋሚ ነበረች፤ አሁን ግን ለእሷ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት ችያለሁ። አሁን አቋማችንን ታከብራለች እንዲሁም በደረሰብን ነገር እንደምታዝንልንና እንደምትደግፈን ትገልጻለች።” ስቬትላና አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ኦርቶዶክስ የሆነችው የ91 ዓመቷ አያቴም በደረሰብን ነገር እንደምታዝንና እንደምታስብልን ሁልጊዜ ትገልጻለች። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት ማሳየት ጀምራለች።”

ስቬትላናን እና አላምን ሁልጊዜ እናስባቸዋለን። ይሖዋ ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት ይዘው መቀጠል እንዲችሉ ‘ልባቸውን እንደሚያጸናው’ እንተማመናለን።—መዝሙር 10:17