በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እህት ታትያና ሾልነር

ሰኔ 21, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ | እህት ታትያና ሾልነር በይሖዋ በመታመን ፈተናን በደስታ እየተቋቋመች ነው

ወቅታዊ መረጃ | እህት ታትያና ሾልነር በይሖዋ በመታመን ፈተናን በደስታ እየተቋቋመች ነው

መስከረም 14, 2022 ዘጠነኛው ጠቅላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ እህት ታትያና ሾልነር ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረበችውን የይግባኝ ጥያቄ ውድቅ አደረገ። እርግጥ እህት ታትያና አሁን ወህኒ አትወርድም።

ታኅሣሥ 16, 2021 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው ፍርድ ቤት ታትያና ያቀረበችውን የይግባኝ ጥያቄ ውድቅ አደረገ።

በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት ሰኔ 25, 2021 እህት ታትያና ሾልነር ጥፋተኛ ናት በማለት በሁለት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት እንድትቀጣ ወስኗል።

አጭር መግለጫ

ታትያና ሾልነር

  • የትውልድ ዘመን፦ 1993 (ቢሮቢድዣን)

  • ግለ ታሪክ፦ አባቷ ገና በሕፃንነቷ ስለሞተ እሷንና ወንድሟን ብቻዋን ያሳደገቻቸው እናቷ ናት። የምትሠራው በመድኃኒት ቤት ውስጥ ነው። በረዶ ላይ መንሸራተት፣ ብስክሌት መንዳትና መረብ ኳስ መጫወት ትወዳለች

    ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት ያደረባት በቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ ልብስ ስፌት እየተማረች በነበረበት ጊዜ ነው። የይሖዋ ምሥክር የሆነች የክፍሏ ልጅ በምታሳየው ባሕርይ ምክንያት ተማርካ ነበር። በ2014 የ12 ዓመት ልጅ የሆነችውን ዘመዷን በሞት ባጣች ጊዜ የትንሣኤ ተስፋ አጽናናት። በ2017 ተጠመቀች

የክሱ ሂደት

የካቲት 6, 2020 በቢሮቢድዣን የሚገኙ የሩሲያ ባለሥልጣናት የ27 ዓመቷን ታትያናን ጨምሮ በስድስት እህቶች ላይ የወንጀል ክስ መሠረቱ። እሷም ሆነች ሌሎቹ እህቶች ሃይማኖታቸውን በማራመዳቸው ብቻ “ጽንፈኞች ናቸው” የሚል ክስ ተመሥርቶባቸዋል። በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ 19 ክሶች ተመሥርተዋል።

ታትያና ይሖዋ ይህን ፈተና እንድትወጣ እየረዳት እንደሆነ እርግጠኛ ናት። እንዲህ ብላለች፦ “ስደቱ በጀመረበት ወቅት መንፈሳዊ ፕሮግራሜ ትንሽ ተስተጓጉሎ ነበር፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቤን አላቋረጥኩም። ስሜቴንና የሚያሳስበኝን ነገር በሙሉ ለይሖዋ እነግረው ነበር። የሚያጋጥመኝን ነገር ሁሉ በጽናት መቋቋምና እስከ መጨረሻው ታማኝ መሆን እንድችል መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠኝ እጸልይ ነበር። በተጨማሪም በፍርድ ቤት ለይሖዋ ስም ጥብቅና መቆም እንድችል ድፍረትና ጥበብ እንዲሰጠኝ ጸልያለሁ።”

አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ አገልጋዮቹን ምንጊዜም እንደሚደግፋቸው፣ እንደሚረዳቸውና እንደሚጠብቃቸው ማወቄ ደስታዬን ለመጠበቅ ረድቶኛል። ይሖዋ ኃያል በሆነው ቀኝ እጁ ይዞኛል። ይህ ደግሞ በእሱ ሙሉ በሙሉ እንድተማመንና ፈተና ሲያጋጥመኝ እንድረጋጋ ረድቶኛል።”—ኢሳይያስ 41:10

ታትያና የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እየተጠባበቀች ባለችበት በዚህ ጊዜ በይሖዋ እርዳታ ‘መከራን በጽናት መቋቋሟን’ እንደምትቀጥል እንተማመናለን።—ሮም 12:12