በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ዲሚትሪ ማሌቫኒ፣ እህት ኦልጋ ኦፓሌቫ፣ እህት ኦልጋ ፓንዩታ እና ወንድም አሌክሲ ትሮፊሞቭ

ሰኔ 29, 2021 | የታደሰው፦ የካቲት 13, 2023
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ—እስራት ተፈረደባቸው | ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በፈተና ውስጥ ቢሆኑም ደስታና ብርታት አግኝተዋል

ወቅታዊ መረጃ—እስራት ተፈረደባቸው | ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በፈተና ውስጥ ቢሆኑም ደስታና ብርታት አግኝተዋል

የካቲት 10, 2023 በፕሪሞርስኪ ክልል የሚገኘው የስፓስክ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ዲሚትሪ ማሌቫኒ፣ እህት ኦልጋ ኦፓሌቫ፣ እህት ኦልጋ ፓንዩታ እና ወንድም አሌክሲ ትሮፊሞቭ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላልፏል። ወንድም ዲሚትሪ ማሌቫኒ የሰባት ዓመት፣ ወንድም አሌክሲ ትሮፊሞቭ የስድስት ዓመት ተኩል፣ እህት ኦልጋ ፓንዩታ ደግሞ የአራት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል። ሦስቱም ከፍርድ ቤት ወዲያውኑ ወደ እስር ቤት ተወስደዋል። እህት ኦልጋ ኦፓሌቫ የአራት ዓመት ተኩል የገደብ እስራት ተበይኖባታል። በአሁኑ ወቅት ወህኒ አትወርድም።

አጭር መግለጫ

ዲሚትሪ ማሌቫኒ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1990 (ስፓስክ-ዳልኒ)

  • ግለ ታሪክ፦ የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ አስተማሪ ነው። ባለቤቱ ኡልያና አርቲስት ነች። በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ እንደሆነና በመሥፈርቶቹ መመራት አርኪ ሕይወት ለመምራት እንደሚያስችል ተገነዘበ። በ2004 ተጠመቀ

ኦልጋ ኦፓሌቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1952 (ስፓስክ-ዳልኒ)

  • ግለ ታሪክ፦ በወጣትነቷ በአምላክ ታምን የነበረ ቢሆንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት አልነበራትም። የ22 ዓመት ወጣት የሆነችው ልጇ ከሞተች ብዙም ሳይቆይ ኦልጋ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው የትንሣኤ ተስፋ ስትማር በጣም ተደሰተች። እምነቷ እያደገ ሲሄድ ያገኘችውን ተስፋ ለሌሎች ማካፈል ጀመረች። በ1995 ተጠመቀች። ከልጅነቷ አንስቶ ሙዚቃና መዝሙር ትወዳለች። በተለይ የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመር ያስደስታታል

ኦልጋ ፓንዩታ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1959 (ኒዥኒ ኖቭጎሮድ)

  • ግለ ታሪክ፦ ጡረታ ከመውጣቷ በፊት የአፀደ ሕፃናት አስተማሪ እና የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኛ ሆና ሠርታለች። በ1982 ከቭላድሚር ጋር ትዳር መሠረተች። ለአካለ መጠን የደረሱ ሁለት ሴት ልጆችና አንድ ወንድ ልጅ አላቸው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስታጠና መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽና ለመረዳት የማይከብድ ትምህርት በመያዙ ልቧ ተነካ። በ1996 ተጠመቀች

አሌክሲ ትሮፊሞቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1959 (ማማካን፣ ኢርኩትስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በቭላዲቮስቶክ የኮሌጅ ተማሪ ሳለ ከታማራ ጋር ተገናኙ፤ በኋላም ትዳር መሠረቱ። አራት ልጆች አፍርተዋል፤ የልጅ ልጆችም አይተዋል። የቁልፍ ሠሪ ነበር፤ በቅርቡ ደግሞ የውኃ ማሞቂያ ማሽኖች መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ ኃላፊ ሆኖ ይሠራ ነበር። የአምላክ ቃል ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት የሚያስችለው እንዴት እንደሆነ ከተማረ በኋላ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ይሖዋን ለማገልገል ወሰነ። በ1996 ተጠመቀ

የክሱ ሂደት

ኅዳር 25, 2018 ሕግ አስከባሪ አካላት በስፓስክ-ዳልኒ ከተማ የሚኖሩ አራት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ሰብረው በመግባት ፈተሹ። ፖሊሶቹ የኦልጋ ኦፓሌቫን በር ለመቁረጥ በኤሌክትሪክ መጋዝ ተጠቅመዋል። ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ በሩን ያልከፈተችው ለምን እንደሆነ ኦልጋን ጠየቋት። እሷ ግን መልስ ልትሰጣቸው አልቻለችም። ፖሊሶቹ አምቡላንስ ጠሩ፤ ከዚያም የልብ ሕመም እንዳጋጠማት ታወቀ። በዚያው ቀን ፖሊሶቹ ኦልጋን ከሆስፒታል አውጥተው ወደ ወንጀል ምርመራ ጣቢያ ወሰዷት። ኦልጋ ባጋጠማት የልብ ሕመም የተነሳ ግራ እጇንና ግራ እግሯን በደንብ መጠቀም አትችልም። የሚንከባከባት ቪታሊ ኢሊኒክ የተባለው ልጇ ሲሆን እሱም ክስ ተመሥርቶበታል።

አራቱም ለሁለት ቀናት ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ተደረገ። ኅዳር 27, 2018 የቁም እስር ተፈረደባቸው። ከአንድ ዓመት በላይ ካለፈ በኋላ ደግሞ የተጣሉባቸው ገደቦች እንዲላሉ ተደረገ።

‘የጽንፈኛ ድርጅትን’ እንቅስቃሴ በማደራጀትና በእንቅስቃሴዎቹ በመካፈል ወንጀል ተከሰዋል።

የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን ጨምሮ ወዳጆቻቸውና ዘመዶቻቸው፣ እንዲህ ያሉ ሰላማዊ ዜጎች በእምነታቸው ምክንያት የሚቀጡት ለምን እንደሆነ እንዳልገባቸው ገልጸዋል። የዲሚትሪ የሥራ ባልደረቦችም እምነቱን ባይጋሩም እንኳ ይደግፉታል፤ እንዲሁም ተስፋ እንዳይቆርጥ ያበረታቱታል።

ዲሚትሪ፣ ስደት ቢደርስበትም ደስተኛ መሆን መቻሉ ይሖዋ ከእሱ ጋር እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ይሰማዋል። እንዲህ ብሏል፦ “የሙሴ በትር ይሖዋ ከእሱ ጋር እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ እንደነበረ ሁሉ እኔም ደስታዬን መጠበቅ መቻሌ ይሖዋ እየደገፈኝ እንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።” በተጨማሪም ደስተኛ መሆኑ “በፍርድ ቤት ለሚሠሩትም ሆነ በምርመራው ለሚካፈሉት ሰዎች ግሩም ምሥክርነት” እንደሚሰጥ ገልጿል።

ኦልጋ ኦፓሌቫም እንዲህ ብላለች፦ “ፈተናውን በጽናት በምቋቋምበት ወቅት የይሖዋን እጅ በተለያዩ መንገዶች አይቻለሁ። ለሁሉም ነገር በይሖዋ መታመን ጀምሬያለሁ፤ ትናንሽ ነገሮችንም ጭምር ለይሖዋ እተዋቸዋለሁ።”

አሌክሲ በማረፊያ ቤትና በቁም እስር በነበረበት ጊዜ ምን እንደረዳው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “[ይሖዋ] ብርቱ እንድሆን ረድቶኛል። ማረፊያ ቤት በገባሁበት ወቅት ይህን ተመልክቻለሁ። ድፍረት እንዲሰጠኝ ይሖዋን ጠየቅኩት። ወዲያውኑ እጄና እግሬ መንቀጥቀጡን አቆመ፤ ድምፄም መርገብገቡን ተወ። አዲሱን ሁኔታዬን ለመልመድ አእምሮዬን አዘጋጀሁ።”

ኦልጋ ፓንዩታ እንዲህ ብላለች፦ “ይህ የይሖዋን ስም የሚመለከት ጉዳይ ነው። ስለዚህ በእሱ መተማመን፣ ለእሱ የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ማቅረብ፣ አቅማችን በፈቀደ መጠን ፈቃዱን ማድረግ እንዲሁም ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ማጠናከር አለብን።”

ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በሚጠባበቁበት ወቅት ‘ዓለታቸው’ የሆነው ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጣቸው ሙሉ በሙሉ መተማመናቸውን እንዲቀጥሉ እንጸልያለን።—ዘዳግም 32:4