ሰኔ 7, 2022 | የታደሰው፦ ሚያዝያ 3, 2023
ሩሲያ
ወቅታዊ መረጃ— እስራት ተፈረደባቸው | ወንድሞቻችን በይሖዋ መታመናቸው ለመጽናት ረድቷቸዋል
መጋቢት 31, 2023 በሞስኮ የሚገኘው የባቡሽኪንስኪ የአውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ኢቫን ቻይኮቭስኪ፣ ወንድም ዩሪ ቼርኒሼቭ፣ ወንድም ቪታሊ ኮማሮቭ፣ ወንድም ሰርጌ ሸታሎቭ እና ወንድም ቫርዳን ዜካርያን ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላልፏል። ኢቫን፣ ዩሪ፣ ቪታሊ እና ሰርጌ እያንዳንዳቸው የስድስት ዓመት ከሦስት ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል። ቫርዳን የአራት ዓመት ከሦስት ወር እስራት ተፈርዶበታል። ሁሉም ከፍርድ ቤት ወደ ወህኒ ተወስደዋል።።
የክሱ ሂደት
ኅዳር 24, 2020
የሩሲያ ባለሥልጣናት በሞስኮ የሚገኙ ቢያንስ 20 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶችን በረበሩ። ፖሊሶች ኢቫንን፣ ዩሪን፣ ቪታሊን እና ሰርጌን ወደ ማረፊያ ቤት ከወሰዷቸው በኋላ ለየብቻ ነጣጥለው አሰሯቸው። የዩሪ ቤት ሲበረበርና እሱና ቤተሰቡ ምርመራ ሲደረግባቸው በቪዲዮ ካሜራ ይቀረጽ ነበር። ይህ ቪዲዮ በኋላ ላይ በመንግሥት የቴሌቪዥን የዜና ጣቢያዎች ተላልፏል
ኅዳር 26, 2020
ሰርጌ ከማረፊያ ቤት ተለቆ የቁም እስረኛ ተደረገ። ቤቱ በተበረበረበት ወቅት በደረሰበት ጉዳት የተነሳ ሆስፒታል ገብቶ የነበረው ቫርዳን ደግሞ ማረፊያ ቤት ውስጥ ለብቻው ተነጥሎ እንዲቆይ ተደረገ
ኅዳር 27, 2020
ፍርድ ቤቱ ኢቫን፣ ዩሪ እና ቪታሊ ከማረፊያ ቤት ተፈትተው የቁም እስረኛ እንዲሆኑ ወሰነ
ኅዳር 30, 2020
ባለሥልጣናቱ ቫርዳን ከማረፊያ ቤት እንዲለቀቅና የቁም እስረኛ እንዲሆን ወሰኑ፤ ቫርዳን ፖሊሶች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በኃይል እንደተጠቀሙ በመግለጽ ለአቃቤ ሕግ ቢሮ ቅሬታ አቀረበ
የካቲት 16, 2022
ክሱ በፍርድ ቤት መታየት ጀመረ
አጭር መግለጫ
ውድ ወንድሞቻችንና ቤተሰቦቻቸው ምንጊዜም ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ጥረት ሲያደርጉ ይሖዋም ወደ እነሱ እየቀረበ መሆኑን ማየታችን በጣም ያበረታታናል።—ያዕቆብ 4:8