በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ሰርጌ እና እህት አና መለኒክ፣ ወንድም ቫለሪ እና እህት ማሪና ሮጎዚን እንዲሁም ወንድም ኢጎር እና እህት ዬቭጌኒያ የጎዛርያን

የካቲት 26, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ | ከሰባት ወራት በላይ ያለፍርድ የታሰሩት ሦስት ወንድሞች ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ነው

ወቅታዊ መረጃ | ከሰባት ወራት በላይ ያለፍርድ የታሰሩት ሦስት ወንድሞች ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ ነው

መጋቢት 18, 2022 የቮልጎግራድ ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም ሰርጌ መለኒክ፣ ወንድም ቫለሪ ሮጎዚን እና ወንድም ኢጎር የጎዛርያን ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። ሦስቱም ወንድሞች በእስር ቤት ይቆያሉ።

መስከረም 23, 2021 የቮልጎግራድ ትራክቶሮዛቮድስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ሦስቱም ወንድሞች ጥፋተኛ ናቸው የሚል ውሳኔ አስተላለፈ። ወንድም ኢጎር የጎዛርያን እና ወንድም ሰርጌ መለኒክ የስድስት ዓመት እስራት ተበይኖባቸዋል። ወንድም ቫለሪ ሮጎዚን ደግሞ የስድስት ዓመት ከአምስት ወር እስራት ተበይኖበታል።

አጭር መግለጫ

ሰርጌ መለኒክ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1972 (ቮልጎግራድ፣ ቮልጎግራድ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት በመኪና ጥገና ሙያ ተመርቋል። በአሁኑ ወቅት ጣሪያ በመሥራት ይተዳደራል። በ1993 ከአና ጋር ትዳር መሠረተ። ሦስት ወንዶች ልጆችን አፍርተዋል። በቤተሰብ ሆነው ተፈጥሮን ማየትና ተራራ መውጣት ይወዳሉ

    አና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ሰርጌ፣ አና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቷ እንዴት እንደለወጣት ሲመለከት እሱም ማጥናት ጀመረ። በ1999 ተጠመቀ

ቫለሪ ሮጎዚን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1962 (ክራስኖካምስክ፣ ፐርም ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ለአሥራ ሁለት ዓመታት የጦር አውሮፕላን አብራሪ ነበር፤ ጡረታ ከወጣ በኋላ መሐንዲስ ሆኖ ሠርቷል። በ1984 ከማሪና ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለት ወንዶች ልጆች አፍርተዋል

    በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ1998 ተጠመቀ

ኢጎር የጎዛርያን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1965 (ቮልጎግራድ፣ ቮልጎግራድ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ጫማ ሠሪ እና የኤሌክትሪክ ባለሙያ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዚቃ ይወዳል። ጊታር ይጫወታል። በ2002 ከዬቭጌኒያ ጋር ትዳር መሠረተ። አንድ ወንድ ልጅ አላቸው

    የአምላክን መንግሥት ምሥራች የነገረችው እናቱ ናት። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አሳማኝና ያልተወሳሰበ መሆኑ ማረከው። በ1992 ተጠመቀ

የክሱ ሂደት

ግንቦት 16, 2019 ፖሊሶች እና የፌዴራል ደህንነት አባላት ሩሲያ ውስጥ በቮልጎግራድ ክልል የሚኖሩ ሰባት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች በረበሩ። ከሁለት ቀናት በኋላ የማዕከላዊ አውራጃ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ወንድም ሰርጌ መለኒክ፣ ወንድም ቫለሪ ሮጎዚን እና ወንድም ኢጎር የጎዛርያን ማረፊያ ቤት ሆነው ፍርዳቸውን እንዲጠባበቁ ወሰነ። ሦስቱ ወንድሞች ለሰባት ወራት በእስር ቆይተዋል።

ሦስቱ ወንድሞች ከቤተሰባቸው ጋር የተቀላቀሉ ቢሆንም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እየተጠባበቁ ባሉበት ወቅት የተለያዩ ችግሮች እያጋጠሟቸው ነው። ወንድም ቫለሪ ያጋጠመውን እንመልከት፤ የሩሲያ ፌዴሬሽን የገንዘብ ዝውውር ቁጥጥር በሚያደርግባቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ የቫለሪ ስም ገብቷል። ቫለሪ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉንም የባንክ ሒሳቦቼን እንዳላንቀሳቅስ ታግጃለሁ፤ እንዲሁም ስልክ እና ኢንተርኔት መጠቀም አይፈቀድልኝም። ሥራዬ ስልክ እና ኢንተርኔት መጠቀም ስለሚጠይቅ ሥራዬን መቀጠል አልቻልኩም።” እሱና ባለቤቱ የዕለት ተዕለት ፍላጎታቸውን ለማሟላት ጡረታቸውን ለመጠቀም ተገድደዋል። ከመሠረታዊ ነገሮች ውጭ ተጨማሪ ነገሮችን ለማድረግ አቅማቸው አይፈቅድም።

በተጨማሪም ሰርጌ እና ኢጎር ፍርድ ቤቱ በጣለባቸው ገደቦች ምክንያት ሥራ ማግኘት ከባድ ሆኖባቸዋል። ሰርጌ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት የሚቀርብ መሆኑ የሥራ ፕሮግራሙን እንዳስተጓጎለበት ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “የምተዳደረው ጣሪያ በመሥራት ነው፤ በፍርድ ቤት ቀጠሮዎች መሃል አንድን ሥራ ጀምሬ መጨረስ እንድችል የምቀበለው ብዙ ጊዜ የማይወስዱ ተባራሪ ሥራዎችን ብቻ ነው።”

ኢጎር ደግሞ የጤና እክል ስላለበት በተደጋጋሚ ሐኪም ቤት መሄድ ያስፈልገዋል። በተጨማሪም ኢጎር “በቀረበብኝ ክስ የተነሳ ፈጽሞ ሥራ ማግኘት አልቻልኩም” ብሏል። ኢጎር የጤና እክልና የገንዘብ ችግር ቢያጋጥመውም እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ ሰጥቶናል፤ ይህ ቤተሰባችንም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እየተንከባከበን ነው።”

ወንድሞቻችን በተጣሉባቸው ገደቦች የተነሳ እነሱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ከባድ ችግር እንዳጋጠማቸው ግልጽ ነው። በሩሲያ የሚኖሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በሙሉ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸው በመተማመን በፈተና ውስጥ በአቋማቸው እንደሚጸኑ እንተማመናለን።—ማቴዎስ 6:33