በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ቪታሊ ኢሊኒክ

ግንቦት 10, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ | ወንድም ቪታሊ ኢሊኒክ ሌሎች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰሉ አበረታቶታል

ወቅታዊ መረጃ | ወንድም ቪታሊ ኢሊኒክ ሌሎች በተዉት ምሳሌ ላይ ማሰላሰሉ አበረታቶታል

ሐምሌ 28, 2022 የፕሪሞርይስ ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም ቪታሊ ኢሊኒክ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አድርጎታል። እርግጥ ወንድም ቪታሊ አሁን ወህኒ አይወርድም።

ሚያዝያ 15, 2022 በፕሪሞርይስ ክልል የሚገኘው የኡሱሪስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ቪታሊ ጥፋተኛ ነው የሚል ብይን ያስተላለፈ ሲሆን የሁለት ዓመት የገደብ እስራት ፈርዶበታል።

አጭር መግለጫ

ቪታሊ ኢሊኒክ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1974 (ኡሱሪስኪ፣ ፕሪሞርይስ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ከፖሊስ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተመርቆ በውስጥ ጉዳዮች ዘርፍ ይሠራ ነበር። ሰዎች የሚሞቱት ለምን እንደሆነና ከሞቱ በኋላ ምን እንደሚያጋጥማቸው ማወቅ ይፈልግ ነበር። በ1990ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ1999 ተጠመቀ። በአሁኑ ጊዜ የመንገድ ጽዳት ሠራተኛ ሆኖ ይሠራል። በ2006 ከባለቤቱ ከኢሪና ጋር ትዳር መሠረተ

የክሱ ሂደት

የካቲት 2019 ፖሊሶች በስፓስክ ዳልኒ ከተማ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከተመሠረተው ክስ ጋር በተያያዘ በወንድም ቪታሊ ኢሊኒክ መኖሪያ ቤት ላይ ፍተሻ አካሄዱ። መስከረም 18, 2019 የሩሲያ ባለሥልጣናት በወንድም ቪታሊ ላይ ምርመራ ማድረግ ጀመሩ። ጥቅምት 23, 2019 ፖሊሶች በድጋሚ ቤቱን የፈተሹ ሲሆን ወንድም ቪታሊን አስረው ለሁለት ቀን ያህል በማረፊያ ቤት እንዲቆይ አደረጉ። ወንድም ቪታሊ ማረፊያ ቤት ሳለ ወደ ይሖዋ ይጸልይ ነበር። በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲያስታውስ “ወደ ይሖዋ ስጸልይ በውስጤ የነበረው ግራ መጋባት ተወግዶ ሰላምና መረጋጋት አገኛለሁ” በማለት ተናግሯል።

ከማረፊያ ቤት ከወጣ በኋላ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ እገዳ ተጥሎበታል። እናቱ እህት ኦልጋ ኦፓሌቫ ደግሞ ሌላ ክስ ተመሥርቶባታል።

ቪታሊ ካጋጠመው ነገር ብዙ ትምህርት አግኝቷል። እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ይሖዋ ከምንችለው በላይ እንድንፈተን እንደማይፈቅድ ድሮም ቢሆን አውቃለሁ። አሁን ግን ይህን እውነታ በገዛ ሕይወቴ ማየት ችያለሁ። የሚደርስብን ችግር እየባሰ በሄደ መጠን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ሸክላ ሠሪያችን ነው፤ በሕይወቴ ውስጥ አንድ ፈተና እንዲደርስብኝ ከፈቀደ ሁኔታውን በመቆጣጠር እኔን ለመቅረጽ ይጠቀምበታል። ፈተናው ከምችለው በላይ እንደሆነ ከተሰማኝ ይሖዋ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ እንዲሰጠኝ እጸልያለሁ።”—2 ቆሮንቶስ 4:7

በተፈጥሮው ዓይናፋር የሆነው ቪታሊ በ1 ጴጥሮስ 5:9 ላይ ማሰላሰሉ ድፍረት እንዲያገኝ ረድቶታል። በተጨማሪም ስደትን በድፍረት እየተጋፈጡ ያሉ በሩሲያ የሚኖሩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ምሳሌ አበረታቶታል። ቪታሊ እንዲህ በማለት በልበ ሙሉነት ተናግሯል፦ “ከቀረበብኝ ክስ ጋር በተያያዘ ይሖዋ የሚፈቅደው ውሳኔ ምንም ሆነ ምን . . . በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በባለሥልጣናት ፊት ምሥክርነት መስጠት መቻሌ ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማኛል።”

እኛም ልክ እንደ ቪታሊ የይሖዋ ሕዝቦች በተዉት የእምነትና የድፍረት ምሳሌ ላይ በማሰላሰል ብርታት ማግኘት እንችላለን። ይሖዋ ‘ፈቃዱን እንድናደርግ በመልካም ነገር ሁሉ ስላስታጠቀን’ እናመሰግነዋለን።—ዕብራውያን 13:20, 21