ሚያዝያ 1, 2021 | የታደሰው፦ የካቲት 17, 2023
ሩሲያ
ወቅታዊ መረጃ—ወንድም ተፈረደበት | የሩሲያ ፍርድ ቤት የወንድም ዬቭጌኒ ዬጎሮቭን ሃይማኖታዊ ነፃነት እየተጋፋ ነው
የካቲት 17, 2023 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ዬቭጌኒ ዬጎሮቭን ጥፋተኛ ነው በማለት የሁለት ዓመት ከስድስት ወር የገደብ እስራት በይኖበታል። እርግጥ አሁን ወህኒ አይወርድም።
ጥቅምት 3, 2022 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው ፍርድ ቤት የዬቭጌኒን የጥፋተኝነት ውሳኔ ሽሮታል። ይህ የሆነው ዘጠነኛው ጠቅላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ ጉዳዩ ወደ አይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል ፍርድ ቤት እንደገና ተልኮ ይግባኙ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲታይ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ ነው። አሁን ጉዳዩ በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል ወደሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት ተልኮ በድጋሚ ይታያል።
ኅዳር 25, 2021 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው ፍርድ ቤት የዬቭጌኒን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል። መጀመሪያ የተላለፈው ፍርድ በዚያው ይጸናል። እርግጥ አሁን ወህኒ አይወርድም።
ሰኔ 21, 2021 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ዬቭጌኒ ዬጎሮቭን ጥፋተኛ ነው በማለት የሁለት ዓመት ከስድስት ወር የገደብ እስራት በይኖበታል።
አጭር መግለጫ
ዬቭጌኒ ዬጎሮቭ
የትውልድ ዘመን፦ 1991 (ቢሮቢድዣን)
ግለ ታሪክ፦ ያሳደጉት እናቱ እና አያቱ ናቸው። የኤሌክትሪክ ምሕንድስና አጥንቷል። ቁልፍ በመሥራትና በጥገና ሥራ ይተዳደራል። ሥነ ጽሑፍ ይወዳል። አንድ ልብ ወለድ መጽሐፍ እንዲሁም የግጥም መድብል አሳትሟል። በ2005 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። መስከረም 2019 ከክሴኒያ ጋር ትዳር መሠረተ። ነሐሴ 2020 ወንድ ልጅ ወለዱ
የክሱ ሂደት
ግንቦት 2018 የፌዴራል ደህንነት አባላት በቢሮቢድዣን ከተማ ሰፊ የፍተሻ ዘመቻ አካሄዱ። ዬቭጌኒ ከማግባቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት፣ እምነቱን በማራመድና መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ “ወንጀል” ተከሰሰ። ከዚያም የጉዞ እገዳ ተጣለበት። የዬቭጌኒ እናት ላሪሳ አርታሞኖቫ የዬቭጌኒ ሠርግ እንዳለፈ ወዲያውኑ ክስ ተመሥርቶባታል። ታኅሣሥ 2019 በቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደቱ ጀመረ።
ዬቭጌኒ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንደቀረበ እንደተሰማው ተናግሯል። “ሁኔታዎች በጣም ከባድ በሆኑበት ወቅት ይሖዋ አረጋግቶኛል፤ እንዲሁም ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ሰጥቶኛል” ብሏል።—2 ቆሮ. 4:7
ዬቭጌኒ የይሖዋ እርዳታ ባይለየውም እንኳ ከፊቱ ለሚጠብቀው ሁኔታ አእምሯዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። እንዲህ ብሏል፦ “ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነገር፣ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ማጠናከሬ ነው።”
ዬቭጌኒን እና ክሴኒያን ጨምሮ በሩሲያ የሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በሙሉ ስደት ቢደርስባቸውም በመዝሙር 10:17 ላይ የሰፈረው የሚከተለው ሐሳብ እንደሚያበረታታቸው እንተማመናለን፦ “ይሖዋ ሆይ፣ የዋሆች የሚያቀርቡትን ልመና ግን ትሰማለህ። ልባቸውን ታጸናለህ፤ ደግሞም ትኩረት ትሰጣቸዋለህ።”