በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም አንድሬ ስቱፕኒኮቭ ከባለቤቱ ከኦልጋ ጋር

ግንቦት 18, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ | ወንድም አንድሬ ስቱፕኒኮቭ በይሖዋ በመታመን የሚደርሱበትን ፈተናዎች በጽናት እየተቋቋመ ነው

ወቅታዊ መረጃ | ወንድም አንድሬ ስቱፕኒኮቭ በይሖዋ በመታመን የሚደርሱበትን ፈተናዎች በጽናት እየተቋቋመ ነው

ነሐሴ 3, 2022 ስምንተኛው ጠቅላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ወንድም አንድሬ ስቱፕኒኮቭ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረበውን የይግባኝ ጥያቄ ውድቅ አደረገ። ወንድም አንድሬ እስር ቤት ይቆያል።

መስከረም 7, 2021 የክራስናያርስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት አንድሬ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ ቀደም ሲል የተላለፈበት ብይን በዚያው እንዲጸና ወሰነ።

ሰኔ 3, 2021 በክራስናያርስክ የሚገኘው የዠለዝኖዶሮዥኒ አውራጃ ፍርድ ቤት አንድሬ ጥፋተኛ ነው በማለት የስድስት ዓመት እስራት ፈረደበት። ወንድም አንድሬ ከፍርድ ቤት ወደ እስር ቤት ወዲያውኑ ተወስዷል።

አጭር መግለጫ

አንድሬ ስቱፕኒኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1973 (ኖሪልስክ፣ ክራስናያርስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በነዳጅ ማውጫ ምሕንድስና ሙያ ሠልጥኗል። በ1993 ከኦልጋ ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለቱም ሥነ ጥበብ እና ከቤት ውጭ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መካፈል ያስደስታቸዋል

    ከወጣትነቱ ጀምሮ ስለ አምላክ ማወቅ ይፈልግ ነበር። የመጀመሪያው የቺቺንያ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት በቺቺኒያ ይኖር የነበረ ሲሆን በዚያ ወቅት አሰቃቂ ነገሮችን ተመልክቷል። መጥፎ ነገሮች የሚደርሱት ለምን እንደሆነና የአምላክን ጥበቃ ማግኘት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ይፈልግ ነበር። እሱና ኦልጋ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙበት መንገድ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ ምክር የሚሰጥ መሆኑ አስደነቃቸው

የክሱ ሂደት

ሐምሌ 3, 2018 የፌዴራል ደህንነት አባላት ወንድም አንድሬ ስቱፕኒኮቭን በክራስናያርስክ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያዙት። በክራስናያርስክ የወንጀል ክስ የተመሠረተበት የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክር እሱ ነው። በቀጣዩ ቀን በክራስናያርስክ የሚገኘው የዠለዝኖዶሮዥኒ አውራጃ ፍርድ ቤት አንድሬ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ወሰነ።

የአንድሬ ባለቤት ኦልጋ እሱን ለማበረታታት ደብዳቤዎችን ትልክለት ነበር። ይሁንና ከባለቤቱ የሚመጡት ደብዳቤዎች በድንገት ሲቋረጡ አንድሬ ስጋት አደረበት። አንድሬ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው መጣና ‘ባለቤትህ ምን ሆና ነው? የምታውቀው ነገር አለ?’ ብሎ ጠየቀኝ።” ይህም የአንድሬን ስጋት አባባሰው። የእስር ቤቱ ኃላፊዎች የባለቤቱን ደብዳቤዎች ሆን ብለው እያስቀሩበት እንደሆነ አንድሬ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አወቀ። እንዲህ ብሏል፦ “ከእነሱ ጋር ለመተባበር ከተስማማሁ ወይም ወንጀለኛ መሆኔን ካመንኩ በቅርቡ ባለቤቴን እንደማገኛት ነገሩኝ።” ሆኖም አንድሬ በይሖዋ በመታመን አቋሙን ፈጽሞ አላላላም። በማረፊያ ቤት ለስምንት ወራት ከቆየ በኋላ አራት ወር በቁም እስር እንዲቆይ ተደረገ።

ሐምሌ 2, 2019 ከቁም እስር ተለቀቀ። ደብዳቤ መቀበልም ሆነ መላክ እንዲሁም ኢንተርኔት መጠቀም አይፈቀድለትም። በተጨማሪም ባለሥልጣናቱ ማነጋገር የሚችላቸውን ሰዎች በተመለከተ እገዳ ጥለውበታል።

አንድሬ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በሚጠባበቅበት ወቅት፣ ራሱን ሲወስን ለይሖዋ ስለገባው ቃል ያስባል፤ እንዲሁም ይህን ቃሉን ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። “ይሖዋን በማወቄ እንዲሁም እሱ ከጎኔ በመሆኑ እኮራለሁ” በማለት በቁርጠኝነት ተናግሯል።

በእርግጥም አንድሬ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው።—መዝሙር 28:7