በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም አሌክሳንደር አኮፖቭ፣ ወንድም ኮንስታንቲን ሳምሶኖቭ እና ወንድም ሻሚል ሱልታኖቭ

ሰኔ 2, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ | ወንድም አኮፖቭ፣ ወንድም ሳምሶኖቭ እና ወንድም ሱልታኖቭ ፈተና ቢደርስባቸውም በይሖዋ ታምነዋል

ወቅታዊ መረጃ | ወንድም አኮፖቭ፣ ወንድም ሳምሶኖቭ እና ወንድም ሱልታኖቭ ፈተና ቢደርስባቸውም በይሖዋ ታምነዋል

ነሐሴ 5, 2022 የስታቭሮፖል ክልል ፍርድ ቤት ወንድም አሌክሳንደር አኮፖቭ፣ ወንድም ኮንስታንቲን ሳምሶኖቭ እና ወንድም ሻሚል ሱልታኖቭ ያቀረቡትን ይግባኝ ተመልክቶ ውሳኔ አስተላልፏል። በአሌክሳንደርና በሻሚል ላይ የተጣለው መቀጮ ወደ 250,000 ሩብል (4,077 የአሜሪካ ዶላር) ተቀይሯል፤ አሁን መቀጮውን መክፈል ይኖርባቸዋል። በኮንስታንቲን ላይ የተበየነው እስራት ወደ 400,000 ሩብል (6,524 የአሜሪካ ዶላር) መቀጮ ተቀይሯል። ወዲያውኑ ከእስር ይፈታል።

ሚያዝያ 19, 2022 በስታቭሮፖል ክልል የሚገኘው የኔፍቴኩምስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት አሌክሳንደር፣ ኮንስታንቲን እና ሻሚል ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላልፏል። አሌክሳንደርና ሻሚል የ500,000 ሩብል (6,055 የአሜሪካ ዶላር) መቀጮ ተፈርዶባቸዋል። ሆኖም በማረፊያ ቤት በመቆየታቸው የተነሳ የገንዘብ መቀጮውን መክፈል አይጠበቅባቸውም። ኮንስታንቲን የሰባት ዓመት ተኩል እስራት ተበይኖበታል። ወዲያውኑ ወደ እስር ቤት ተወስዷል።

አጭር መግለጫ

አሌክሳንደር አኮፖቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1992 (ኔፍቴኩምስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ከአባቱና ከታላቅ ወንድሙ ጋር በግንባታ ሥራ ተሰማርቷል። እግር ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ እና ቴኒስ ይወዳል፤ እንዲሁም ተፈጥሮን ማድነቅና ምግብ ማብሰል ያስደስተዋል

    በ2007 በ14 ዓመቱ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ

ኮንስታንቲን ሳምሶኖቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1977 (ኔፍቴኩምስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ወጣት ሳለ ቼዝና የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ያስደስተው ነበር። በአሁኑ ወቅት በአንድ ሆስፒታል ውስጥ የኮምፒውተር ሲስተም መሐንዲስ ሆኖ ይሠራል። እሱና ባለቤቱ ስቬትላና በ1998 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። በ2000 ተጠመቁ። አንድ ልጅ አላቸው

ሻሚል ሱልታኖቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1977 (ማህሙድ መክተብ፣ ስታቭሮፖል ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ሕንፃዎችን በመጠገን ሙያ ተሰማርቷል። በ2000ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ2003 ተጠመቀ። በ2004 ከኤሌና ጋር ትዳር መሠረተ። ከቀድሞ ትዳሯ ያፈራችውን ልጅ አብሯት አሳድጓል

የክሱ ሂደት

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 26, 2017 መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች በኔፍቴኩምስክ አቅራቢያ በሚገኝ ሐይቅ ዳርቻ እየተዝናኑ የነበሩ 18 የይሖዋ ምሥክሮችን በቁጥጥር ሥር አዋሉ። ልጆችንና አረጋውያንን ጨምሮ ሁሉንም በአውቶቡስ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከወሰዷቸው በኋላ ለሦስት ሰዓታት ያህል ምርመራ አደረጉባቸው። በኋላም በኔፍቴኩምስክ የሚገኙ በርካታ ወንድሞችና እህቶች የፖሊስ ክትትል ይደረግባቸው ጀመር፤ ቤታቸውም ተበርብሯል። ከጊዜ በኋላ አሌክሳንደር አኮፖቭ፣ ኮንስታንቲን ሳምሶኖቭ እና ሻሚል ሱልታኖቭ ተይዘው ለአንድ ዓመት ያህል በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ተደረገ።

አሌክሳንደር የጭንቀት ችግርና የጤና እክል ስላለበት መታሰር ይፈራ እንደነበር ተናግሯል። የእስር ቤት ቆይታውን ለመቋቋም የሚያስችል አእምሯዊና ስሜታዊ ጥንካሬ እንዲሰጠው ወደ ይሖዋ ምልጃ አቀረበ። አሌክሳንደር እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታው ከአቅሜ በላይ እንደሆነብኝ በመግለጽ ወደ ይሖዋ የጸለይኩባቸው በርካታ ጊዜያት ነበሩ። አንድ ዓመት [ገደማ] ማረፊያ ቤት ውስጥ በጽናት እንደቆየሁ ሳስበው ለማመን ይከብደኛል።” አሌክሳንደር መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት በማይችልበት ጊዜ ጥቅሶችን እንዲያስታውስ በመርዳት ይሖዋ ጸሎቱን መልሶለታል። የሚያስታውሰውን ጥቅስ ሁሉ ወረቀት ላይ ይጽፍ ነበር፤ ከዚያም በየጠዋቱ አንዱን ጥቅስ በማንበብ ያ ጥቅስ ያለበትን ሁኔታ ለመቋቋም የሚረዳው እንዴት እንደሆነ ያስብ ነበር። እንዲህ ማድረጉ ከእስራቱ ጋር በተያያዘ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረው ረድቶታል።

ኮንስታንቲን ድፍረት ማግኘት የቻለው ባለቤቱ በየጊዜው ከምትጽፍለት ደብዳቤዎች ነው። በአንዱ ደብዳቤ ላይ ባለቤቱ፣ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች እንደ ታሪካዊ አጋጣሚዎች አድርጎ እንዲመለከታቸው አበረታታችው። ኮንስታንቲን እንዲህ ብሏል፦ “የተናገረችው ነገር አስገርሞኝ ነበር፤ በኋላ ግን ሁኔታው የምር እየቀለለኝ መጣ።”

ሻሚል በማረፊያ ቤት ባሳለፋቸው የመጀመሪያ ወራት ሁኔታው በጣም ከብዶት እንደነበረ ተናግሯል። ሆኖም እንዲህ ብሏል፦ “ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እየቀለለኝ መጣ። ይህም ይሖዋ እንዳልተወኝ አረጋግጦልኛል።” በታሰረበት ወቅት፣ ወደፊት ስለሚያጋጥሙት ፈተናዎች ከልክ በላይ ባለመጨነቅ በይሖዋ እንደሚታመን ማሳየት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ተምሯል።

ሦስቱም ወንድሞች የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባቸዋል፤ እንዲሁም ስልክም ሆነ ኢንተርኔት መጠቀም አይፈቀድላቸውም። በእነዚህ ገደቦች የተነሳ አሌክሳንደር የሚያስፈልገውን ሕክምና ማግኘት ከባድ ሆኖበታል፤ ኮንስታንቲንም የኮምፒውተር ፕሮግራመርነት ሥራውን ማከናወን አልቻለም። እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች ቢኖሩም ወንድሞቻችን ለአምላካቸው ታማኝ ለመሆን ቆርጠዋል።

ይሖዋ በእሱ የሚታመኑትን እነዚህን ወንድሞች እንደሚባርካቸው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 20:7