በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም አላም አሊዬቭ፣ ወንድም ቫሊሪ ክሪገር፣ ወንድም ሰርጌ ሹልያሬንኮ እና ወንድም ዲሚትሪ ዛጉሊን

መጋቢት 18, 2021 | የታደሰው፦ ታኅሣሥ 20, 2022
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ—ወንድሞች ተፈረደባቸው | በቢሮቢድዣን የሚኖሩ አራት ወንድሞች እስራት ሊፈረድባቸው ይችላል

ወቅታዊ መረጃ—ወንድሞች ተፈረደባቸው | በቢሮቢድዣን የሚኖሩ አራት ወንድሞች እስራት ሊፈረድባቸው ይችላል

በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት በወንድም አላም አሊዬቭ፣ በወንድም ቫሊሪ ክሪገር፣ በወንድም ሰርጌ ሹልያሬንኮ እና በወንድም ዲሚትሪ ዛጉሊን ላይ የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፏል። ወንድም አሊዬቭ የስድስት ዓመት ተኩል፣ ወንድም ዛጉሊን ደግሞ የሦስት ዓመት ተኩል እስራት ተፈርዶባቸዋል። ወንድም ክሪገር እና ወንድም ሹልያሬንኮ የሰባት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል። አራቱም ወንድሞች ከፍርድ ቤት ወዲያውኑ ወደ ወህኒ ተወስደዋል።

አጭር መግለጫ

አላም አሊዬቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1963 (ልያኪ መንደር፣ አዘርባጃን)

  • ግለ ታሪክ፦ ጀርመን ውስጥ በሶቪየት ኅብረት ጦር ሠራዊት ውስጥ አገልግሏል። ከጊዜ በኋላ በዓሣ ማጥመጃ ጀልባ ላይ ሠርቷል። በ1989 ወደ ካባረቭስክ፣ ሩሲያ ተዛወረ። በአሁኑ ወቅት ፋብሪካ ውስጥ ይሠራል

    ወደ ሩሲያ ከመጣ ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ1991 ተጠመቀ። በ2015 ከስቬትላና ጋር ትዳር መሠረተ። ባልና ሚስቱ ከቤት ውጭ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች መካፈል ያስደስታቸዋል

ቫሊሪ ክሪገር

  • የትውልድ ዘመን፦ 1968 (የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ያደገው ሃይማኖተኛ ባልሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ልጅ እያለ አክሮባት ይወድ ነበር። በእሽት የሚሰጥ ሕክምና የተማረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዚህ ሙያ በግሉ ይሠራል። በ1994 ተጠመቀ። በ2017 ከናታሊያ ጋር ትዳር መሠረተ። ባልና ሚስቱ መረብ ኳስ መጫወትና ከቤት ውጭ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች አብረው መካፈል ያስደስታቸዋል

ሰርጌ ሹልያሬንኮ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1984 (ካባረቭስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ አባቱ ጦር ሠራዊት ውስጥ በሚያገለግልበት ወቅት ቱርክሜኒስታን ተመድቦ ስለነበር ቫሊሪ ልጅ እያለ በዚያ ኖሯል። ፋብሪካ ውስጥ በረዳትነት ይሠራ ነበር። ሥዕል መሣል እና የሌላ አገር ቋንቋ መማር ይወዳል። ስለ ይሖዋ የተማረው ከእናቱ ነው። በ1997 በ13 ዓመቱ ተጠመቀ

ዲሚትሪ ዛጉሊን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1973 (ካባረቭስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ልጅ እያለ ወታደር ለመሆን ይመኝ ነበር። የማርሻል አርት እና የፓራሹት ሥልጠና አግኝቷል። በአሁኑ ወቅት በባቡር ድርጅት ውስጥ ይሠራል። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረው በ1991 ነው። በ1992 ተጠመቀ። በ2012 ከታትያና ጋር ትዳር መሠረተ

የክሱ ሂደት

ግንቦት 17, 2018 በቢሮቢድዣን የሚገኙ 150 የደህንነት ባለሥልጣናት “የፍርድ ቀን” የሚል ስያሜ የተሰጠው የፍተሻ ዘመቻ አካሄዱ። ወንድም አላም አሊዬቭ “የጽንፈኛ ድርጅትን እንቅስቃሴዎች በማደራጀት” ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን ለስምንት ቀናት ያህል ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ። በወንድም ቫሊሪ ክሪገር፣ በወንድም ሰርጌ ሹልያሬንኮ እና በወንድም ዲሚትሪ ዛጉሊን ላይም ክስ ተመሠረተባቸው። አራቱም ወንድሞች አካባቢውን ለቀው እንዳይሄዱ ገደብ ተጥሎባቸዋል። የወንድም አላም፣ የወንድም ቫሊሪ እና የወንድም ዲሚትሪ የትዳር ጓደኞችም ለብቻቸው ክስ የተመሠረተባቸው መሆኑ እነዚህን ወንድሞች ይበልጥ አስጨንቋቸዋል።

ወንድም አላም በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት ስለ ስደት በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አድርጎ ነበር። ያነበበውን ነገር ለጉባኤው አባላትም አካፍሏቸዋል። እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞችና እህቶች ስደት ሲደርስባቸው ለፍርሃት እጅ እንዳይሰጡ አበረታታኋቸው። ይህ ማበረታቻ ወቅታዊ ነበር፤ ምክንያቱም ልክ ከአንድ ሳምንት በኋላ በጉባኤያችን ያሉ 21 ቤተሰቦች ቤታቸው በፖሊስ ተፈተሸ።”

ቫሊሪ እና ባለቤቱ ናታሊያ የጉዞ ገደብ ስለተጣለባቸው በሶል፣ ደቡብ ኮሪያ በተደረገ የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ መገኘት አልቻሉም። ከዚህም ሌላ በእስራኤል የሚኖሩትን ወላጆቹን ሄደው መጠየቅ አልተፈቀደላቸውም። የሚያሳዝነው አባቱ የካቲት 2019 አረፉ። ይህ ከመሆኑ ከጥቂት ወራት በፊት እናቱ አከርካሪያቸው ላይ ቀዶ ጥገና አድርገው ነበር፤ በመሆኑም ቋሚ እንክብካቤ ያስፈልጋቸው ነበር። ቫሊሪ ይሖዋ የሚያስፈልገውን እርዳታ እንደሰጣቸው ይሰማዋል። ወላጆቹ የይሖዋ ምሥክሮች ባይሆኑም እንኳ እናቱን የተንከባከቧቸው በእስራኤል የሚኖሩ መንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ናቸው። እንዲህ ብሏል፦ “የእናቴን ጉዳይ አንስተን ወደ ይሖዋ ጸለይን፤ ይሖዋም ጸሎታችንን መልሶልናል። በእስራኤል የሚኖሩ የእምነት ባልንጀሮቻችን እናቴን አበረታተዋታል እንዲሁም አጽናንተዋታል። እየሄዱ ይጠይቋት፣ ያጫውቷት እንዲሁም ስብሰባዎች ላይ እንድትገኝ ይጋብዟት ነበር። እኛ ራሳችን እናቴን ሄደን መጠየቅ ባንችልም በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር በኩል የይሖዋን እጅ አይተናል።”

ወንድም ዲሚትሪ ይህ ስደት ድሮም የሚያውቀውን ነገር ይበልጥ እንዳረጋገጠለት ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “በሕይወታችን ውስጥ ሁሉ ነገር በሰመረበት እና ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ ላይ ምንም ዓይነት ገደብ ባልተጣለበት ወቅት ለመንፈሳዊ ሀብታችን ያለን አድናቆት ይቀንስና ችላ እንለው ይሆናል። ሆኖም መንግሥት አምላክን በነፃነት እንዳናመልክ እገዳ ሲጥልብን አሁን ያለንን ነገር በአግባቡ መጠቀም እና ሊያጋጥመን ለሚችል ስደት መዘጋጀት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን። በአሁኑ ጊዜ ያለንን የአምልኮ ነፃነት ‘በሰማይ ሀብት ለማከማቸት’ መጠቀም የጥበብ እርምጃ ነው። ይህን ማድረጋችን እስከ መጨረሻው ለመጽናት እንዲሁም ጠንካራ እምነት ይዘን ለመቀጠል ይረዳናል።”—ማቴዎስ 6:20

ይሖዋ በሩሲያ ለሚኖሩ ውድ ወንድሞቻችን “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነውን] ኃይል” እየሰጣቸው እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።—2 ቆሮንቶስ 4:7