ሐምሌ 26, 2022 | የታደሰው፦ ታኅሣሥ 6, 2023
ሩሲያ
ወቅታዊ መረጃ—ወንድሞች ተፈረደባቸው | ጸሎት ብርታት ሆኗቸዋል
ታኅሣሥ 5, 2023 በሃንቲ ማንሲስክ ራስ ገዝ ክልል በዩግራ የሚገኘው የሱርጉት ከተማ ፍርድ ቤት በ17 ወንድሞችና በአንዲት እህት ላይ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላለፈ። ከእነዚህ ወንድሞች መካከል ወንድም ቭያችዬስላቭ ቦሮኖስ፣ ወንድም ሳቭዬሊ ጋርጋሊክ፣ ወንድም ዬቭግዬኒ ካይርያክ፣ ወንድም አርተም ኪም፣ ወንድም ሰርጌ ሎግዬኖቭ፣ ወንድም አሌክሲ ፕልዬኮቭ እና ወንድም ሰርጌ ቮሎስኒኮቭ ይገኙበታል። አሥራ ሰባቱ ወንድሞች ከስድስት ዓመት ከሦስት ወር አንስቶ እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ የገደብ እስራት ተፈርዶባቸዋል። እህት ደግሞ የሦስት ዓመት ከሦስት ወር የገደብ እስራት ተጥሎባታል። በአሁኑ ወቅት ወህኒ አይወርዱም።
የክሱ ሂደት
የካቲት 15, 2019
ፖሊሶች በሱርጉትና በአቅራቢያው ባሉ ከተሞች የሚኖሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ። ከዚያም ሰርጌ ሎግዬኖቭን ጨምሮ ሦስት ወንድሞች ወደ ማረፊያ ቤት ተወሰዱ። አንድ ሌላ ወንድም ደግሞ በኋላ ላይ ወደ ሥነ አእምሮ ሆስፒታል እንዲሄድ ታዘዘ። በዚህ ዜና ላይ የተጠቀሱት ሰባት ወንድሞች ስለ እምነት አጋሮቻቸው መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንግልት ደርሶባቸዋል
የካቲት 26, 2019
የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ሰርጌ ሎግዬኖቭ የሕክምና እርዳታ ማግኘት እንዲችል ከእስር እንዲለቀቅ ለሩሲያ መንግሥት ትእዛዝ አስተላለፈ
ሚያዝያ 11, 2019
ሰርጌ ሎግዬኖቭ ከማረፊያ ቤት ተለቀቀ
ጥቅምት 29, 2021
ክሱ በፍርድ ቤት መታየት ጀመረ
አጭር መግለጫ
ደፋር የሆኑ ወንድሞቻችን የሚደርስባቸውን መከራ እየተጋፈጡ ባሉበት ወቅት ይሖዋ ጸሎታቸውን እንደሚሰማና ጭንቅ ውስጥ ሲሆኑ ፈጥኖ እንደሚደርስላቸው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 69:17