በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፣ የላይኛው መደዳ፦ ወንድም ዩሪ ጌራስኮቭ፣ ወንድም ማክሲም ኻልቱሪን፣ ወንድም ቭላዲሚር ኮሮቤኒኮቭ እና ወንድም አንጄይ ኦኒስጁክ። የታችኛው መደዳ፦ ወንድም አንድሬ ሱቮርኮቭ፣ ወንድም ዬቭጌኒ ሱቮርኮቭ እና ወንድም ቭላድሚር ቫሲሌቭ

ሚያዝያ 22, 2021
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ—ይግባኙ ውድቅ ተደረገ | ለወራት ያህል በማረፊያ ቤትና በቁም እስር እንዲቆዩ የተደረጉት ወንድሞቻችን ጸሎት፣ ጥናትና ከሌሎች ያገኙት ማበረታቻ እንዲጸኑ እየረዳቸው ነው

ወቅታዊ መረጃ—ይግባኙ ውድቅ ተደረገ | ለወራት ያህል በማረፊያ ቤትና በቁም እስር እንዲቆዩ የተደረጉት ወንድሞቻችን ጸሎት፣ ጥናትና ከሌሎች ያገኙት ማበረታቻ እንዲጸኑ እየረዳቸው ነው

ጥቅምት 4, 2022 የኪሮቭ ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም ማክሲም ኻልቱሪን፣ ወንድም ቭላዲሚር ኮሮቤኒኮቭ፣ ወንድም አንጄይ ኦኒስጁክ፣ ወንድም አንድሬ ሱቮርኮቭ፣ ወንድም ዬቭጌኒ ሱቮርኮቭ እና ቭላድሚር ቫሲሌቭ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አድርጎታል። እርግጥ አሁን ወህኒ አይወርዱም።

ሰኔ 3, 2022 በኪሮቭ የሚገኘው የፒርቮማይስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ማክሲም ኻልቱሪን፣ ቭላዲሚር ኮሮቤኒኮቭ፣ አንጄይ ኦኒስጁክ፣ አንድሬ ሱቮርኮቭ፣ ዬቭጌኒ ሱቮርኮቭ እና ቭላድሚር ቫሲሌቭ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላልፏል። ከሁለት ዓመት ተኩል እስከ ስድስት ዓመት ተኩል የሚደርስ የገደብ እስራት ፈርዶባቸዋል። ወንድም ዩሪ ጌራስኮቭ የፍርድ ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት ሕይወቱ ቢያልፍም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ነው የሚል ብይን አስተላልፎበታል።

አጭር መግለጫ

ዩሪ ጌራስኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1956 (አዘርባጃን)

  • የሞተበት ቀን፦ ሚያዝያ 24, 2020

  • ግለ ታሪክ፦ ከልጅነቱ አንስቶ ኳስ መጫወትና ፎቶ ማንሳት ያስደስተው ነበር። በትልቅ የኦርኬስትራ ቡድን ውስጥ ሠርቷል። በአዘርባጃን በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የተነሳ በ1993 ወደ ሩሲያ ሄዶ መኖር ጀመረ። በ2011 ከአሌቭቲና ጋር ትዳር መሠረተ። በዚያው ዓመት ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። እሱና ባለቤቱ በእግር መንሸራሸርና ጓደኞቻቸውን መጠየቅ ያስደስታቸው ነበር

ማክሲም ኻልቱሪን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1974 (ኪሮቭ፣ ኪሮቭ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ከልጅነቱ አንስቶ ማንበብ ይወድ ነበር። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት ያደረበት በ1993 ነው። በ1995 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። አረጋዊ ወላጆቹን ይንከባከባል። ወላጆቹ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ቢሆኑም እምነቱን ይደግፉለታል

ቭላዲሚር ኮሮቤኒኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1952 (ዲክሰን ደሴት፣ ክራስኖያርስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ አባቱ በአርክቲክ ውቅያኖስ ላይ ምርምር የሚያደርግ ሳይንቲስት ነበር። ቭላዲሚር ልጅ ሳለ ትናንሽ ቅርጻ ቅርጾችን መሥራት ይወድ ነበር። የቧንቧ ሠራተኛና የማሽን ባለሙያ ሆኖ ሠርቷል። አሁን ጡረታ የወጣ ሲሆን ዓሣ ማጥመድ ያስደስተዋል

    እሱና ባለቤቱ ኦልጋ በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። በተለይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ትኩረቱን ሳቡት። በ1996 ተጠመቀ። እሱና ቤተሰቡ (ወንድ ልጃቸውንና ሴት ልጃቸውን ጨምሮ) የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ተግባራዊ በማድረጋቸው በመካከላቸው ያለው ዝምድና ተጠናክሯል

አንጄይ ኦኒስጁክ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1968 (ቢያሊስቶክ፣ ፖላንድ)

  • ግለ ታሪክ፦ በወጣትነቱ እግር ኳስ መጫወትና ክብደት ማንሳት ያስደስተው ነበር። በ1990 ተጠመቀ። በ1997 ወደ ኪሮቭ ተዛውሮ እዚያ መኖር ጀመረ። የሩሲያን ሥነ-ጽሑፍ ይወዳል። በ2002 ከአና ጋር ትዳር መሠረተ። እሱና ባለቤቱ ወጣ ብለው መዝናናት፣ እንጉዳይ መሰብሰብና እግር ኳስ መጫወት ይወዳሉ

አንድሬ ሱቮርኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1993 (ኪሮቭ፣ ኪሮቭ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ እናቱ ከሕፃንነቱ አንስቶ እውነትን አስተምራዋለች። ልጅ ሳለ ሳይንስ ማጥናትና በስፖርታዊ ጨዋታዎች መካፈል በተለይ ደግሞ መረብ ኳስ መጫወት ያስደስተው ነበር። በ2007 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ በዕፅ ሱሰኞች ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ ሠርቷል። በ2016 ከባለቤቱ ከስቬትላና ጋር ትዳር መሠረተ። እሱና ባለቤቱ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ያስደስታቸዋል

ዬቭጌኒ ሱቮርኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1978 (ኩሜኒ፣ ኪሮቭ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ልጅ ሳለ ቼዝና ሆኪ መጫወት እንዲሁም ሙዚቃ ማዳመጥ ይወድ ነበር። የኤሌክትሪክ ባለሙያ ነው። በ16 ዓመቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ1995 ተጠመቀ። በ18 ዓመቱ በወታደራዊ አገልግሎት ምትክ ሌላ ሥራ እንዲሰጠው ጠየቀ። ስድስት ጊዜ ለፍርድ ከቀረበ በኋላ በመጨረሻ ሕዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ተፈቀደለት። በ2000 ስቬትላናን ያገባ ሲሆን ልጇን አንድሬን (ከላይ የተጠቀሰውን) አብረው አሳድገዋል

ቭላድሚር ቫሲሌቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1956 (ፐርም)

  • ግለ ታሪክ፦ ልጅ ሳለ እግር ኳስ መጫወት ያስደስተው ነበር። የቧንቧ ሠራተኛ እና ሾፌር ሆኖ ሠርቷል። አሁን ጡረታ ወጥቷል። እሱና ባለቤቱ ናዴዥዳ በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ቭላድሚር በ1994 ተጠመቀ

የክሱ ሂደት

ጥቅምት 9, 2018 የኪሮቭ ፖሊሶች 14 የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ፈተሹ። በውጤቱም ወንድም ማክሲም ኻልቱሪን፣ ወንድም ቭላዲሚር ኮሮቤኒኮቭ፣ ወንድም አንጄይ ኦኒስጁክ፣ ወንድም አንድሬ ሱቮርኮቭ እና ወንድም ዬቭጌኒ ሱቮርኮቭ ተያዙ። በኋላም በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ተደረጉ። ጥር እና ሐምሌ 2019 ላይ ደግሞ ወንድም ቭላድሚር ቫሲሌቭ እና ወንድም ዩሪ ጌራስኮቭ ክስ ተመሠረተባቸው።

ቭላዲሚር ኮሮቤኒኮቭ ከሁለት ወር ለሚበልጥ ጊዜ በማረፊያ ቤት ቆየ። ከዚያም በቁም እስር ሆኖ የታመመች ባለቤቱንና ሴት ልጃቸውን እንዲንከባከብ ተወሰነ። ማክሲም እና አንድሬ ከሦስት ወር ለሚበልጥ ጊዜ፣ ዬቭጌኒ ለአምስት ወር ገደማ፣ አንጄይ ደግሞ ለ327 ቀናት በማረፊያ ቤት ቆይተዋል። ከእነዚህ ወንድሞች መካከል አብዛኞቹ አሁን የቁም እስረኛ ሆነዋል። ከማረፊያ ቤት ቢለቀቁም ከአካባቢያቸው መውጣት አይፈቀድላቸውም።

ወንድሞች በማረፊያ ቤት ሳሉ ከቤተሰቦቻቸው መለየት ከብዷቸው ነበር። ሆኖም ይሖዋ ቤተሰቦቻቸውን እንደሚንከባከብላቸው እርግጠኞች ነበሩ።

ለምሳሌ ያህል፣ የቭላዲሚር ኮሮቤኒኮቭ ባለቤት ኦልጋ የአካል ጉዳተኛ ናት። ወንድም ቭላድሚር “በጣም የከበደኝ የአካል ጉዳተኛ የሆነችውን ባለቤቴን ብቻዋን ትቼ መሄዴ ነው” ብሏል። በተጨማሪም ቤታቸው በተፈተሸበት ወቅት ስልኳን ስለወሰዱት ሁኔታዋ አሳስቦት ነበር። ሆኖም አንዲት እህት፣ ወንድሞችና እህቶች ባለቤቱን እየተንከባከቧት እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ ስትልክለት በጣም ተጽናና። በኋላም ባለቤቱ ኦልጋ ደህንነቷን የሚገልጽ የሚያጽናና ደብዳቤ ላከችለት።

ወንድሞች በእንቅስቃሴያቸው ላይ ገደብ መጣሉና “ጽንፈኛ” ተብለው መፈረጃቸው ተጨማሪ ችግር ፈጥሮባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጥሩ ሥራ ማግኘት ከባድ ሆኖባቸዋል። በተጨማሪም የባንክ ሒሳባቸውን መጠቀም አይችሉም።

ያም ሆኖ ዬቭጌኒ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ አትረፍርፎ ሰጥቶናል። በምድረ በዳ እንደነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ እኛም ምንም ነገር አልጎደለብንም። የይሖዋ ቤተሰብ በቁሳዊ፣ በስሜታዊና በመንፈሳዊ ሁኔታ የሚያደርግልንን ድጋፍ በደንብ ማየት ችለናል።”

ወንድሞች ጸሎት፣ የግል ጥናትና የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ታማኝና ደፋር እንዲሆኑ እንደረዳቸው ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ቭላድሚር ቫሲሌቭ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙት ዘገባዎች ከይሖዋ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር እንደሌለ አስገንዝበውናል። ይህም በአምላክ ላይ ያለን እምነት እንዲጠናከርና ከበፊቱ ይበልጥ በእሱ እንድንታመን አስችሎናል።”

የክስ ሂደቱ በውድ ወንድሞቻችን እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከባድ ሁኔታ ቢፈጥርባቸውም በይሖዋ መታመናቸውን እንደሚቀጥሉ እርግጠኞች ነን። “ሰው” ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትልባቸው እንደማይችል ስለሚያውቁ ጸንተው ይቆማሉ።—መዝሙር 56:4