ጥር 27, 2020 | የታደሰው፦ የካቲት 9, 2024
ሩሲያ
ወቅታዊ መረጃ—ይግባኙ ውድቅ ተደረገ | የሩሲያ ፍርድ ቤት በወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭ፣ በእህት ቨነራ ዱሎቫ እና በእህት ዳርያ ዱሎቫ ላይ ፍርድ አስተላለፈ
የካቲት 8, 2024 የስቬርድሎቭስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት፣ የወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭን እና የእህት ቨነራ ዱሎቫን ይግባኝ ውድቅ አድርጎታል። ቀደም ሲል የተላለፈባቸው የገደብ እስራት አሁን ተፈጻሚ ይሆናል። ብይኑ አሁን ወህኒ እንዲገቡ የሚጠይቅ አይደለም። ፍርድ ቤቱ፣ እህት ዳርያ ዱሎቫን በነፃ አሰናብቷታል፤ ምክንያቱም የተከሰሰችበት ነገር በተፈጸመበት ወቅት ገና 18 ዓመት አልሆናትም ነበር፤ በመሆኑም ለአካለ መጠን ካልደረሱ ልጆች ጋር በተያያዘ የይርጋ ጊዜ አቆጣጠርን በሚደነግገው ሕግ መሠረት ተጠያቂ አትሆንም።
መጋቢት 14, 2023 የሩሲያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ወንድም አሌክሳንደር ፕሪያኒኮቭ እንዲሁም እህት ቨነራ ዱሎቫ እና እህት ዳርያ ዱሎቫ ከተመሠረተባቸው ክስ ነፃ እንዲሆኑ የተላለፈውን ፍርድ ሽሮታል። በመሆኑም ጉዳያቸው ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ተመልሷል።
መጋቢት 15, 2022 የስቬርድሎቭስክ ክልላዊ ፍርድ ቤት በአሌክሳንደር እንዲሁም በቨነራ እና በልጇ በዳርያ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ቀለበሰ። ሆኖም ሦስቱም በተመሠረተባቸው ሌላ ክስ ጥፋተኛ ናቸው ተብሎ ሊፈረድባቸው ይችላል።
የካርፒንስክ ከተማ ፍርድ ቤት በአሌክሳንደር፣ በቨነራ እና በዳርያ ላይ ጥር 27, 2020 ፍርድ አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ በአሌክሳንደር ላይ የሁለት ዓመት ተኩል፣ በቨነራ ላይ የሁለት ዓመት እንዲሁም በዳርያ ላይ የአንድ ዓመት የገደብ እስራት በይኗል። ይህ ፍርድ እነዚህ የይሖዋ አገልጋዮች በቀጥታ እስር ቤት እንዲገቡ የሚያደርግ ባይሆንም እንኳ የተፈረደባቸው ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ ጥብቅ ክትትል እየተደረገባቸው ይቆያሉ። ውሳኔውን አስመልክቶ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ታውቋል።