በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን በኦርዮል ወደሚገኘው የዤሌዝኖዶሮዥኒ አውራጃ ፍርድ ቤት ሲወሰድ

ሐምሌ 31, 2019
ሩሲያ

ወቅታዊ መረጃ—ዴኒስ ክሪስተንሰን ወህኒ ከወረደ በኋላም አቋሙን አላላላም

ወቅታዊ መረጃ—ዴኒስ ክሪስተንሰን ወህኒ ከወረደ በኋላም አቋሙን አላላላም

ወንድም ዴኒስ ክሪስተንሰን ይግባኙ ውድቅ ከተደረገ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይኸውም ሰኔ 6, 2019 የሩሲያ ባለሥልጣናት በኦርዮል ከሚገኘው ማረፊያ ቤት በልጎፍ ከተማ ወደሚገኘው ወህኒ ቤት አዛውረውታል። ልጎፍ የዴኒስ ቤተሰቦችና ወዳጆቹ ከሚኖሩባት ከኦርዮል 200 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ትገኛለች።

ዴኒስ ወህኒ ቤት እንደደረሰ ብዙዎች የሰደቡት ከመሆኑም ሌላ አቋሙን እንዲያላላ ለማድረግ ሞክረዋል። ያም ቢሆን ዴኒስ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ብርቱና ደፋር መሆኑን አሳይቷል።—1 ጴጥሮስ 5:10

ፊንላንድ ውስጥ (ከግራ ወደ ቀኝ)፦ የበላይ አካል አባል የሆነው ማርክ ሳንደርሰን፣ አይሪና ክሪስተንሰን እና በፊንላንድ የሚኖረው ቶሚ ካውኮ

የዴኒስ ባለቤት የሆነችው አይሪና፣ ዴኒስ ከታሰረበት ጊዜ አንስቶ የወንድሞች ፍቅራዊ እንክብካቤና ድጋፍ አልተለያትም። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰንና ኃላፊነት ያላቸው ሌሎች ወንድሞች ሰኔ ወር ላይ አይሪናን ፊንላንድ አግኝተው አበረታተዋታል።

ዴኒስ ወህኒ ከወረደ ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል። አይሪና እሱን በቀን አንዴ በስልክ ለማናገር በቅርቡ ፈቃድ አግኝታለች። ወደ ወህኒ ቤቱ ሄዳ እንድትጠይቀውም ተፈቅዶላታል።

አይሪና ዴኒስ የላከላትን አበረታች ደብዳቤዎች ደጋግማ ስታነብ

ዴኒስና አይሪና እሱ በእስር በቆየባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ብዙ መከራ ቢያሳልፉም ጽኑና ደስተኛ ናቸው። አይሪና እንደገለጸችው ከሆነ ዴኒስ በየሳምንቱ የሚልክላት ደብዳቤዎች በጣም አበረታተዋታል። ከምትወዳቸው ደብዳቤዎች መካከል አንዱ “ለስኬት ቁልፉ አዎንታዊ መሆን ነው፤ ደስተኛ የምንሆንበት ብዙ ምክንያት አለን” የሚል ሐሳብ ይዟል። ዴኒስ ደብዳቤውን ሲደመድም እንዲህ ብሏል፦ “የተፈጠርነው የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመደገፍ ነው። ጉዟችን ረጅም እንደሆነና ገና ድል እንዳልተቀዳጀን አውቃለሁ። ሆኖም ድል ማድረጋችን አይቀርም። ይህን መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ።”

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ሌት ሐምሌ 21 ዴንማርክ ውስጥ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ዴኒስ የጻፈውን ደብዳቤ አንብቦ ነበር፤ ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ ጋር ብሰበሰብ ደስ ይለኝ ነበር፤ ሆኖም የተሰጠኝን የአገልግሎት ምድብ ስላላጠናቀቅኩ መምጣት አልችልም። ወደፊት ግን እንገናኛለን፤ ያንን ቀን በጉጉት እየጠበቅኩ ነው።”

ጳውሎስ በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “እናንተን ባስታወስኩ ቁጥር ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ ይህን የማደርገው ስለ እያንዳንዳችሁ ምልጃ ባቀረብኩ ጊዜ ሁሉ ነው። ደግሞም ምንጊዜም ምልጃ የማቀርበው በደስታ ነው፤ . . . በእስራቴም ሆነ ለምሥራቹ ስሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ ስጥር ከእኔ ጋር የጸጋው ተካፋዮች የሆናችሁት እናንተ በልቤ ውስጥ ናችሁ።”—ፊልጵስዩስ 1:3, 4, 7