ጥር 17, 2020
ሩሲያ
ወንድም ማርኪን እና ወንድም ትሮፊሞቭ እስከ ስድስት ዓመት ተኩል የሚደርስ እስር ሊበየንባቸው ይችላል
ከወንድም ሮማን ማርኪን እና ከወንድም ቪክቶር ትሮፊሞቭ ጋር በተያያዘ የሩሲያ ፍርድ ቤት ጥር 22, 2020 ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል። አቃቤ ሕጉ እስከ ስድስት ዓመት ተኩል የሚደርስ እስር እንዲበየንባቸው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል።
በእነዚህ ሁለት ወንድሞች ላይ እየደረሰ ያለው ስደት የጀመረው መሣሪያ የታጠቁና ጭምብል ያጠለቁ የሩሲያ ልዩ ኃይሎች በፖሊያርኒ ከተማ የሚገኙትን የወንድሞቻችንን ቤቶች ሚያዝያ 18, 2018 በበረበሩበት ወቅት ነበር። ፖሊሶቹ በሌሊት ወደ ወንድም ማርኪን ቤት መጥተው በሩን ሰብረው ገቡ። ከዚያም በያዙት አውቶማቲክ መሣሪያ ወንድም ማርኪንን በማስፈራራት መሬት ላይ እንዲተኛ ካደረጉ በኋላ ቤቱን መፈተሽ ጀመሩ። በወቅቱ ቤት ውስጥ የነበረችው የወንድም ማርኪን የ16 ዓመት ልጅም መሬት ላይ ተኝታ ራሷን በእጆቿ ሸፍና ነበር።
በዚያ ምሽት በፖሊያርኒ ከተማ የሚገኙ የሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች አራት ቤቶችም ተፈትሸዋል። ፖሊሶቹ ወንድም ማርኪንን እና ወንድም ትሮፊሞቭን ጨምሮ ከአሥር የሚበልጡ ወንድሞችንና እህቶችን ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው። ከዚያም በሙርማንስክ የሚገኘው የፖሊያርኒ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ማርኪን እና ወንድም ትሮፊሞቭ ፍርድ እስኪበየንባቸው ድረስ በእስር እንዲቆዩ ወሰነ። እነዚህ ወንድሞች ወደ ስድስት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ እስር ቤት ከቆዩ በኋላ ለተጨማሪ አራት ወራት በቁም እስር ቆይተዋል። የካቲት 7, 2019 ፍርድ ቤቱ ከቁም እስር እንዲለቀቁ ወሰነ። በአሁኑ ወቅት በቁም እስር ላይ ባይሆኑም ፍርድ እስከሚበየንባቸው ጊዜ ድረስ በሚያደርጉት ጉዞ እና የመረጃ ልውውጥ ላይ ገደብ ተጥሏል።
ሩሲያ ውስጥ የወንጀል ፍርድ የሚጠብቃቸው ወደ 300 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ሁሉም ወንድሞችና እህቶች ምንም ነገር ከይሖዋ ፍቅር ሊለያቸው እንደማይችል በመተማመን ደፋር እና ብርቱ ሆነው እንዲቀጥሉ እንጸልያለን።—ሮም 8:38, 39