ሐምሌ 27, 2023
ሩሲያ
ወንድም ሰርጌይ ክሊሞቭ ከሩሲያ እስር ቤት ተፈታ
ሐምሌ 26, 2023 ወንድም ሰርጌይ ክሊሞቭ በአስትራካን ከተማ ከሚገኝ የሩሲያ እስር ቤት ተፈታ፤ ሰርጌይ እስር ቤት አምስት ዓመት ገደማ አሳልፏል። መጀመሪያ በቁጥጥር ሥር የዋለው ሰኔ 3, 2018 ሲሆን ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት ማረፊያ ቤት ቆይቷል። ኅዳር 5, 2019 ተፈረደበት፤ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የጉልበት ሥራ ወደሚሠራበት ወህኒ ቤት ተዛወረ።
ሰርጌይ እስር ቤት እያለ ለዘጠኝ ወር ያህል ባለቤቱን ዩሊያን ማየት አልተፈቀደለትም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከተላኩለት ደብዳቤዎች አብዛኞቹ አልደረሱትም። በእስር ቤት ክፍሉ ውስጥ በነበረው መጥፎ ሁኔታ የተነሳ ለጤና ችግር ተዳርጓል። ሰርጌይ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ሆኖም እንኳ ጸሎትንና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የመሰሉ መንፈሳዊ ልማዶቹን ይዞ መቀጠሉ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረው ረድቶታል።
ባለሥልጣናቱ ሰርጌይ ባለው ሃይማኖታዊ እምነት ምክንያት በጽንፈኝነት ከስሰውታል። ሆኖም ክሱ በፍርድ ቤት በታየበት ወቅት ሰርጌይ ይህ ክስ ሐሰት መሆኑን በድፍረት የገለጸ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች የሚያካፍልበትን ምክንያት እንዲህ በማለት አስረድቷል፦ “አምላኬ ይሖዋ፣ አፍቃሪና ፍትሐዊ አምላክ ነው። ሌሎችን ለመርዳት የሚያነሳሳኝ ፍቅር እንጂ ጥላቻ ወይም ጽንፈኝነት አይደለም።”
ሰርጌይ እና ዩሊያ በድጋሚ ለመገናኘት በመብቃታቸው የደስታቸው ተካፋይ ነን። ሰርጌይ ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ ይሖዋ ስለባረከለትም አመስጋኞች ነን።—ኢያሱ 24:14