ጥር 19, 2021
ሩሲያ
ወንድም ሰርጌ ብሪትቪን እና ወንድም ቫዲም ሌቭቹክ ያቀረቡት ይግባኝ ውድቅ ቢደረግም ከአቋማቸው ፍንክች አላሉም
ጥር 19, 2021 የኬሜሮቮ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም ሰርጌ ብሪትቪን እና ወንድም ቫዲም ሌቭቹክ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል። በመሆኑም መጀመሪያ ላይ የተፈረደባቸው የአራት ዓመት እስራት ይጸናል። እነዚህ ወንድሞች ፍርዳቸውን እየተጠባበቁ የታሰሩበትና በቁም እስረኝነት ያሳለፉት ጊዜ ሲታሰብ ከተፈረደባቸው አራት ዓመት ውስጥ ከሦስት ዓመት በላይ የሚሆነውን ጨርሰዋል። በመሆኑም አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሊፈቱ ይችላሉ። ሁለቱም በአቋማቸው ለመጽናትና በእስር የሚያሳልፉትን ጊዜ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ቆርጠዋል።
መጀመሪያ ጉዳያቸው በታየበት ወቅት በይሖዋ ላይ ስላላቸው እምነት እና እሱን ማገልገላቸው ስላስገኘላቸው ጥቅም ለፍርድ ቤቱ በድፍረት ተናግረዋል።
ሰርጌ እንዲህ ብሏል፦ “አቃቤ ሕጉ እኔ ምን እንዳደርግ ነው የሚፈልገው? እምነቴን እንድክድ ነው? የተሻለ ሰው እንድሆንና ጥሩ የሩሲያ ዜጋ እንድሆን የረዳኝ ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት ነው። አምላክ ትዳሬን እንድታደግና የተሻለ ሕይወት እንዲኖረኝ ስለረዳኝ አመስጋኝ ነኝ። የሕይወትን ዓላማ እንዳውቅና አስደሳች የወደፊት ተስፋ እንዲኖረኝ ስላደረገኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። በሕይወቴ ውስጥ ከምንም ነገር በላይ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ከይሖዋ አምላክ ጋር ለመሠረትኩት የጠበቀ ወዳጅነት ነው። የሚሰነዘርብኝ ማንኛውም የሐሰት ክስ ከእሱ ጋር ያለኝን ወዳጅነት እንዲያበላሽብኝ አልፈቅድም።”
ቫዲም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ የክስ ሂደት ወቅት ሁሉ የተለየ የመረጋጋት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ ከጎኔ እንደሆነ እኔም ከእሱ ጎን እንደሆንኩ አውቃለሁ! የሚፈረድብኝ ፍርድ ምንም ይሁን ምን ዋናው ነገር አምላክ ለእኔ ያለው አመለካከት ነው። አምላክን የሚያስደስቱትን እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ደግነት፣ እምነት፣ ገርነትና ራስን መግዛት ያሉ ባሕርያትን ማፍራቴን እስከቀጠልኩ ድረስ የሚፈረድብኝ ፍርድ ለውጥ አያመጣም።”