ታኅሣሥ 7, 2022
ሩሲያ
ወንድም ሰርጌ ፖልያኮቭ ከሩሲያ እስር ቤት ተፈታ
ወንድም ሰርጌ ፖልያኮቭ ኅዳር 30, 2022 የሦስት ዓመት ፍርዱን አጠናቅቆ ከእስር ቤት ተለቅቋል። ሐምሌ 4, 2018 ለመጀመሪያ ጊዜ ከታሰረበት አንስቶ የተለያየ ዓይነት እስራት አሳልፏል፤ በአንድ ወቅት ለአምስት ወራት ብቻውን ታስሯል።
ሰርጌ የመጨረሻዎቹን 16 ወራት ያሳለፈው ቫልዴይ ከተማ በሚገኝ ወህኒ ቤት ነው፤ ወህኒ ቤቱ የሚገኘው ከመኖሪያው 3,000 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ነው። ሰርጌ ታስሮ በነበረበት ወቅት በጠንካራ እምነቱ የሚታወቅ ሰው ነበር፤ የወህኒ ቤቱን ሠራተኞችና አብረውት የታሰሩ ሰዎችን አክብሮትም አትርፏል። ወህኒ ቤት በነበረው ቆይታ ከቤተሰቦቹና ከወዳጆቹ የሚላኩለት ደብዳቤዎች ብርታት ሆነውታል። በቀን ውስጥ የሚደርሰው ደብዳቤ ብዛት በወህኒ ቤቱ ያሉት 250 ሰዎች በድምሩ ከሚደርሳቸው ደብዳቤ ይበልጣል።
ሰርጌ እንደተለቀቀ ከባለቤቱ ከአነስቴዥያ ጋር ተገናኝቷል። እሷም ለአምስት ወራት ለብቻዋ ታስራ ነበር። በኋላም የፍርድ ቤት ብይኗን ሰማች፤ እምነቷ የሚላትን በማድረጓ የገደብ እስራት ተፈረደባት። በ2017 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ ወንጀል የሚያደርግ ብይን ካስተላለፈ በኋላ መጀመሪያ የታሰሩት ባልና ሚስት ሰርጌና አነስቴዥያ ናቸው።
ሩሲያና ክራይሚያ ውስጥ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ ከ100 በላይ ወንድሞችና እህቶች አሉ። ይሖዋ “[በእሱ] ፊት ንጹሕ ሕሊና” ለመያዝ ሲሉ ‘መከራና ግፍ የሚችሉ’ አገልጋዮቹን እንደሚደግፋቸው እንተማመናለን።—1 ጴጥሮስ 2:19