በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም ኒኮላይ ፖለቮዶቭ እና ወንድም ስታኒስላቭ ኪም ከፍርድ ቤቱ ውጭ ሆነው፣ ጥቅምት 2019

ጥር 31, 2020
ሩሲያ

ወንድም ስታኒስላቭ ኪም እና ወንድም ኒኮላይ ፖለቮዶቭ በሁለት የሩሲያ ፍርድ ቤቶች ክስ ተመሥርቶባቸዋል፤ የመጀመሪያው ብይን የካቲት 4, 2020 ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል

ወንድም ስታኒስላቭ ኪም እና ወንድም ኒኮላይ ፖለቮዶቭ በሁለት የሩሲያ ፍርድ ቤቶች ክስ ተመሥርቶባቸዋል፤ የመጀመሪያው ብይን የካቲት 4, 2020 ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል

የካባረቭስክ ከተማ የዢለዝናዳሮዥኒይ ፍርድ ቤት የካቲት 4, 2020 በወንድም ስታኒስላቭ ኪም እና በወንድም ኒኮላይ ፖለቮዶቭ ላይ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል። አቃቤ ሕጉ ወንድም ኪም እና ወንድም ፖለቮዶቭ እያንዳንዳቸው የሦስት ዓመት እስራት እንዲበይንባቸው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል። የሚያስገርመው ሁለቱም ወንድሞች በዚያው ከተማ በሚገኘው ኢንደስትሪያል አውራጃ ፍርድ ቤት ሌላ የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ጉዳያቸው እየታየ ነው።

ወንድም ኪም እና ወንድም ፖለቮዶቭ የተያዙት ኅዳር 10, 2018 ነበር። በዚያ ቀን በካባረቭስክ ከተማ የሚኖሩ ከ50 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች አንድን ካፌ ተከራይተው እየተዝናኑ ነበር። በወቅቱ ሃይማኖታዊ ስብሰባ እያካሄዱ አልነበረም። የመዝናኛ ፕሮግራሙ ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ በርካታ አድማ በታኝ ፖሊሶችና መርማሪዎች ወደ ካፌው ገብተው እዚያ የነበሩትን ሰዎች እስር ቤት ወሰዱ። ወንድም ኪም እና ወንድም ፖለቮዶቭ እንዲሁም ወንድም ቪታሊ ዙክ ከሁለት ወራት በላይ ያለፍርድ ታስረው ነበር፤ ከዚያም ለበርካታ ወራት በቁም እስር ቆይተዋል።

የካቲት 4 የሚተላለፈው ውሳኔ ወንድም ኪምን እና ወንድም ፖለቮዶቭን ብቻ የሚመለከት ሲሆን ክስ የተመሠረተባቸው በዚያ ፕሮግራም ላይ በመሳተፋቸው ምክንያት ነው። ሆኖም ባለሥልጣናቱ በወንድም ኪም፣ በወንድም ፖለቮዶቭ እና በወንድም ዙክ እንዲሁም በፕሮግራሙ ላይ በተገኙ ሌሎች ሦስት እህቶች ላይ ሌላ ክስ መሥርተዋል። ወንድም ኪምና ወንድም ፖለቮዶቭ ይሄኛው ክስ የተመሠረተባቸው ፕሮግራሙን አዘጋጅታችኋል በሚል ነው። ለዚህ ክስ ብይን የሚሰጥበት ጊዜ አልተወሰነም።

ወንድም ኪምና ወንድም ፖለቮዶቭ ያጋጠማቸው ሁኔታ ለየት ያለ ነው፤ በተመሳሳይ ወቅት ሁለት ክስ ተመሥርቶባቸዋል። መርማሪዎቹ ሁለቱ ክሶች በተለያዩ ፍርድ ቤቶች እንዲታዩ በመወሰናቸው ምክንያት ወንድም ኪምና ወንድም ፖለቮዶቭ በካባረቭስክ ከተማ በሚገኙ ሁለት የተለያዩ ፍርድ ቤቶች ጉዳያቸውን ለመከታተል ተገደዋል።

ሁለቱም ወንድሞች ባለትዳሮች ከመሆናቸውም ሌላ ራሳቸውን ያልቻሉ ልጆች አሏቸው። ይሖዋ ለእነዚህ ውድ ወንድሞቻችንና ለቤተሰቦቻቸው ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ልባቸውንና አእምሯቸውን እንደሚጠብቅላቸው እንዲሁም ይህን ፈተና በታማኝነት ለመወጣት እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—ፊልጵስዩስ 4:7