በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ቪታሊ ፖፖቭ እና ባለቤቱ ናታሊያ

ግንቦት 20, 2021
ሩሲያ

ወንድም ቪታሊ ፖፖቭ በእምነቱ ምክንያት እስራት ሊፈረድበት ይችላል

ወንድም ቪታሊ ፖፖቭ በእምነቱ ምክንያት እስራት ሊፈረድበት ይችላል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ወንድም ቪታሊ ፖፖቭ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ

የካቲት 16, 2022 ስምንተኛው ጠቅላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ወንድም ቪታሊ ፖፖቭ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። እርግጥ ቪታሊ አሁን ወህኒ አይወርድም።

ሐምሌ 23, 2021 የኖቮስብሪስክ አውራጃ ፍርድ ቤት ቪታሊ ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ ከዚህ በፊት የተበየነበት የሦስት ዓመት የገደብ እስር እንዲጸና ወስኗል።

ግንቦት 21, 2021 በኖቮስብሪስክ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ቪታሊ ጥፋተኛ ነው የሚል ውሳኔ አሳለፈ። ቪታሊ የሦስት ዓመት የገደብ እስራት ተፈርዶበታል።

አጭር መግለጫ

ቪታሊ ፖፖቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1967 (ኖቮስብሪስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ የኤሌክትሪክ እና የብየዳ ባለሙያ ሆኖ ይሠራ ነበር። በሶቪየት የጦር ሠራዊት ውስጥ አገልግሏል። የበረዶ ላይ ሸርተቴ፣ እግር ኳስና መረብ ኳስ መጫወት እንዲሁም መዝፈን ይወዳል። ሁለት ወንድሞችና ሁለት እህቶች አሉት። ቪታሊ ወጣት እያለ ታላቅ ወንድሙና እህቱ በአደጋ ሕይወታቸውን አጡ። በመሆኑም ቪታሊ ስለ ሞትና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብዙ ጥያቄዎች ተፈጠሩበት

    በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ሰዎች የሚሞቱበትን ምክንያት በተመለከተ አጥጋቢ መልስ አገኘ። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የተመለከተው ፍቅርና አክብሮት እንዲሁም እርስ በርስ የሚደጋገፉ መሆኑ ልቡን ነካው። በ1994 ተጠመቀ። በ2011 ከናታሊያ ጋር ትዳር መሠረተ

የክሱ ሂደት

ሰኔ 27, 2019 ባለሥልጣናቱ በቪታሊ ላይ የወንጀል ክስ መሠረቱ። ሚያዝያ 9, 2020 ፖሊሶች ወደ ቤቱ መጥተው ለምርመራ ወሰዱት። ከአራት ሰዓት ለሚበልጥ ጊዜ ምርመራ ተካሄደበት።

ቪታሊ አገሪቱ ጽንፈኛ ብላ በፈረጀቻቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተተ። በመሆኑም የባንክ ሒሳቡ ታገደ። ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ሥራውን እንዲለቅቅ ተገደደ። ይህም በቤተሰቡ ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ጫና አሳድሯል።

ይሖዋ የቪታሊን ቤተሰብ መንከባከቡን ቀጥሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎታችንን በሙሉ አሟልቶልናል፤ እንዲሁም አበረታቶናል። ቤተሰቤ በሙሉ ይሖዋ ላደረገልን ነገር አመስጋኝ ናቸው፤ ይህም የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ነገር ለመወጣትና አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ረድቶናል።”

ቪታሊ እነዚህን ፈተናዎች ለመቋቋም የረዳውን ቁልፍ ነገር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበሬ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይሖዋ እውን ሆኖልኛል። ምንም ነገር ቢያጋጥመኝ በእሱ መታመንን ተምሬያለሁ።” ቪታሊ የቤተሰብ አምልኮ የማድረግ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የመገኘትና ሐሳብ የመስጠት፣ አዘውትሮ በአገልግሎት የመካፈል እንዲሁም ልባዊ ጸሎት የማቅረብ ልማድ አለው። “እንዲህ ዓይነት ልማድ ባይኖረኝ ኖሮ በይሖዋ መታመን እና ፈተናውን መወጣት አልችልም ነበር” ብሏል።

በቪታሊ ላይ የሚተላለፈውን ብይን በምንጠባበቅበት ጊዜ ወንድማችንን በጸሎት እናስበዋለን። ‘ኃይልን የሚሰጠን’ አምላካችን ይሖዋ ስደትን በድፍረትና በጽናት እየተቋቋሙ ያሉትን በሩሲያ የሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በሙሉ ማጠናከሩን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—ፊልጵስዩስ 4:13