በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሞስካሌንኮ ከእስር ከተፈታ በኋላ ከፍርድ ቤቱ ውጭ ቆሞ

መስከረም 4, 2019
ሩሲያ

ወንድም ቫለሪ ሞስካሌንኮ ከእስር ተፈታ

ወንድም ቫለሪ ሞስካሌንኮ ከእስር ተፈታ

የካባረቭስክ ክልል የዢለዝናዳሮዥኒይ አውራጃ ፍርድ ቤት መስከረም 2, 2019 ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ ወንድም ቫለሪ ሞስካሌንኮ ለሁለት ዓመት ከሁለት ወር ማኅበረሰባዊ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲሁም ለተጨማሪ ስድስት ወራት ጥብቅ ክትትል እንዲደረግበት በይኗል። ሆኖም ከዚህ በኋላ እስር ቤት መቆየት አያስፈልገውም።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ወንድም ሞስካሌንኮ ከእስር ተለቀቀ፤ በዚህም ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ በጣም ተደስተዋል። ወንድም ሞስካሌንኮ ከነሐሴ 2, 2018 አንስቶ በእስር ቆይቷል። ከመታሠሩ በፊት ረዳት የባቡር ነጂ ሆኖ ይሠራ የነበረ ሲሆን የታመሙ እናቱንም ይንከባከብ ነበር። ወንድም ሞስካሌንኮ ጥብቅ ክትትል የሚደረግበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ ከካባረቭስክ ክልል ውጭ መጓዝ አይፈቀድለትም፤ እንዲሁም በየወሩ ፖሊስ ጣቢያ ሄዶ ወንጀል አለመፈጸሙን ሪፖርት ማድረግ ይጠበቅበታል።

ወንድም ሞስካሌንኮ ነሐሴ 30 ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት የተናገረው የመደምደሚያ ሐሳብ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከሰፈረው የአምላክ ፈቃድ ጋር የሚቃረን ነገር ማድረግ ጨርሶ የማላስበው ነገር ነው። ደግሞም ምንም ዓይነት ጫና ወይም ቅጣት ቢደርስብኝ፣ እንዲያውም ሞት እንኳ ቢፈረድብኝ የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ የሆነውን ይሖዋ አምላክን አልክድም።”

የአውሮፓ የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር ተወካይ የሆነው ያሮስላቭ ሲቩልስኪ እንዲህ ብሏል፦ “ቫለሪ ጥፋተኛ ነው ተብሎ የተፈረደበት በመሆኑ ባንስማማም ወደ ቤቱ መመለስ በመቻሉ ደስ ብሎናል።”

ከወንድም ሞስካሌንኮ በተጨማሪ በካባረቭስክ ክልል የሚኖሩ ሌሎች ሰባት ወንድሞች ለተመሠረተባቸው ክስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እየተጠባበቁ ነው።

ወንድም ሞስካሌንኮ በእስር በቆየበት ወቅት እምነቱ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ስለረዳው ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነታቸው ምክንያት ስደት እየደረሰባቸው ላሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብርታት መስጠቱን እንዲቀጥል እንጸልያለን።—ኢሳይያስ 40:31