በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም አሌክሲ ቤርቹክ እና ባለቤቱ አና፤ ወንድም ዲሚትሪ ጎሊክ እና ባለቤቱ ክርስቲና

መጋቢት 9, 2021
ሩሲያ

ወንድም አሌክሲ ቤርቹክ እና ወንድም ዲሚትሪ ጎሊክ በብላጎቭዬሸዬንስኪይ ከተማ ሊፈረድባቸው ይችላል

ወንድም አሌክሲ ቤርቹክ እና ወንድም ዲሚትሪ ጎሊክ በብላጎቭዬሸዬንስኪይ ከተማ ሊፈረድባቸው ይችላል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ

የካቲት 16, 2022 ዘጠነኛው ጠቅላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ወንድም አሌክሲ ቤርቹክ እና ወንድም ዲሚትሪ ጎሊክ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። ሁለቱም እስር ቤት ይቆያሉ።

መስከረም 2, 2021 የአሙር ክልላዊ ፍርድ ቤት አሌክሲ እና ዲሚትሪ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። በአሌክሲ ላይ የተላለፈው ፍርድ በዚያው ጸና፤ ሆኖም ፍርድ ቤቱ በዲሚትሪ ላይ የተላለፈውን እስራት በአሥር ወር ቀንሶለታል። ወንድሞች ከማረፊያ ቤት ወደ እስር ቤት እንዲዛወሩ ተደረገ።

የሩሲያ ፍርድ ቤት በሁለት ወንድሞች ላይ እስራት ፈረደባቸው፤ ይህ ከ2017 ወዲህ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተፈረደው ረጅሙ እስራት ነው

ሰኔ 30, 2021 በአሙር ክልል የሚገኘው የብላጎቭዬሸዬንስኪይ ከተማ ፍርድ ቤት አሌክሲ ስምንት ዓመት፣ ዲሚትሪ ደግሞ ሰባት ዓመት እንዲታሰሩ ውሳኔ አሳልፏል። ሩሲያ ውስጥ ድርጅታችን በ2017 ከታገደ በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከዚህ ቀደም የተበየነው ረጅም የእስር ፍርድ ሰባት ዓመት ተኩል ነበር። ወንድም አሌክሲ እና ወንድም ዲሚትሪ ወዲያውኑ ከፍርድ ቤት ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።

አጭር መግለጫ

አሌክሲ ቤርቹክ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1975 (ካርታሊ፣ ቼልያቢንስክ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በግንባታና በአናጺነት ሠርቷል። በ1990ዎቹ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ከዚያም ዓመፅ በሚንጸባረቅባቸው ስፖርቶች መካፈሉን ተወ፤ በአሁኑ ወቅት ከጓደኞቹ ጋር እግር ኳስ መጫወት ያስደስተዋል። በ1998 ተጠመቀ። በ2008 ከአና ጋር ትዳር መሠረተ።

ዲሚትሪ ጎሊክ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1987 (ቶሆይ፣ ቡሪያቲያ ሪፑብሊክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ከቻይንኛ ወደ ሩሲያኛ አስተርጓሚ ሆኖ ይሠራል። ክብደት ማንሳት፣ እግር ኳስ መጫወት እና ጊታር መጫወት ያስደስተዋል

    በ1990ዎቹ መላው ቤተሰቡ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ2002 ተጠመቀ። ለውትድርና አገልግሎት ሲመለመል አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት ጥያቄ አቀረበ። በመሆኑም በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ እንዲሠራ ተመደበ። በ2012 ከክርስቲና ጋር ትዳር መሠረተ። አገልግሎታቸውን ለማስፋት ሲሉ እንግሊዝኛና ቻይንኛ እየተማሩ ነው

የክሱ ሂደት

በ2018 መጀመሪያ አካባቢ የመንግሥት ባለሥልጣናት በወንድም ጎሊክ መኖሪያ ቤት ውስጥ የድምፅ እና የቪዲዮ መቅረጫ መሣሪያ በድብቅ አስቀመጡ። ሰኔ 2018 የፌደራል ደህንነት አባላት በብላጎቭዬሸዬንስኪይ የሚገኙ የሰባት የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች በረበሩ። ከዚያም በወንድም አሌክሲ ቤርቹክ እና በወንድም ዲሚትሪ ጎሊክ ላይ የወንጀል ክስ ተመሠረተ። የተከሰሱት የጽንፈኝነት እንቅስቃሴን በማደራጀት ወንጀል ነው።

አሌክሲ የወንጀል ክስ እንደተመሠረተበት ወዲያውኑ አልተነገረውም ነበር። ጥር 21, 2019 በዶሞድዬዶቮ ሞስኮ የአየር ማረፊያ የፓስፖርት ቁጥጥር ክፍል ተያዘ። ከዚያም የፌደራል ደህንነት ከፍተኛ ባለሥልጣን አሌክሲን ወደ መኖሪያ ከተማው ይዞት ተመለሰ፤ አሁንም ድረስ የጉዞ ገደብ ተጥሎበታል።

ሁለቱም ወንድሞች ለስደት አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ። ዲሚትሪ እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታዎች መልካም እንደሚሆኑ ተስፋ ብናደርግም ለስደት መዘጋጀቱ ግን አስፈላጊ ነው። በስደት ወቅት ምን እንደምናደርግ መዘጋጀታችን ጠቅሞናል። ይበልጥ የጠቀመን ግን በመንፈሳዊ ሁኔታ ዝግጅት ማድረጋችን ነው። በስደት ወቅት ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ብልጥ መሆናችን ወይም ከአሳዳጆቻችን መደበቅ መቻላችን ሳይሆን ለአምላክ ታማኝ መሆናችን ነው። ኢየሱስም ቢሆን ጠላቶቹ እንዳያገኙት መደበቅ ይችል ነበር፤ ግን ዓላማው እሱ አልነበረም። እኛም የእሱ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ግባችን ከችግር መሸሽ ሳይሆን ችግሮች ሲያጋጥሙን በድፍረት መጽናት ነው።”

አሌክሲ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “‘እኔ ስደት አይደርስብኝም’ ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ይሖዋ ስደት እንዲደርስብን እንደፈቀደ ግልጽ ነው። ይህን አምነን ከተቀበልን እና አዎንታዊ አመለካከት ካዳበርን ስደት ሲደርስብን ሁኔታውን መቀበልና በይሖዋ ተማምነን በጽናት መቋቋም ቀላል ይሆንልናል።”

አሌክሲን፣ ዲሚትሪንና ሚስቶቻቸውን ጨምሮ በሩሲያ የሚገኙ ወንድሞቻችን በሙሉ “እነሆ፣ አምላክ ረዳቴ ነው፤ ይሖዋ እኔን ከሚደግፉ ጋር ነው” የሚለውን የመዝሙራዊውን ሐሳብ ማስተጋባታቸውን እንደሚቀጥሉ እንተማመናለን።—መዝሙር 54:3, 4