በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም አሌክሳንደር ቦንዳርቹክ እና ባለቤቱ ኤሌና (በስተግራ) እንዲሁም ወንድም ሰርጌ ያቩሽኪን እና ባለቤቱ ታቲያና (በስተቀኝ)

ሚያዝያ 2, 2021
ሩሲያ

ወንድም አሌክሳንደር ቦንዳርቹክ እና ወንድም ሰርጌ ያቩሽኪን ለረጅም ጊዜ በቁም እስር ከቆዩ በኋላ ውሳኔ ሊተላለፍባቸው ነው

ወንድም አሌክሳንደር ቦንዳርቹክ እና ወንድም ሰርጌ ያቩሽኪን ለረጅም ጊዜ በቁም እስር ከቆዩ በኋላ ውሳኔ ሊተላለፍባቸው ነው

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ይግባኛቸውን ውድቅ አደረገ

የካቲት 16, 2022 የኬሜሮቮ ክልላዊ ፍርድ ቤት ወንድም አሌክሳንደር ቦንዳርቹክ እና ወንድም ሰርጌ ያቩሽኪን ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። እርግጥ አሁን ወህኒ አይወርዱም።

በኬሜሮቮ ክልል የሚገኘው የዛቮድስኮይ አውራጃ ፍርድ ቤት፣ ሰኔ 22, 2021 አሌክሳንደር እና ሰርጌ ጥፋተኛ ናቸው በማለት በአራት ዓመት የገደብ እስራት እንዲቀጡ ወሰነ።

አጭር መግለጫ

አሌክሳንደር ቦንዳርቹክ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1974 (ቶፕኪ፣ ኬሜሮቮ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በ19 ዓመቱ አባቱን በሞት አጣ። ትምህርት ቤት ገብቶ ከባድ ማሽኖችን ማንቀሳቀስ ተማረ። በኋላም የአናጢነት ሞያ ተማረ። አሁን የብረት ማቅለጫ ማሽኖችን የመጠገን ሥራ ይሠራል። ዓሣ ማጥመድ፣ በረዶ ላይ መንሸራተት፣ ብስክሌት መንዳትና መሮጥ ያስደስተዋል

  • በ1992 ባለቤቱን ኤሌናን አገባ። ከቤተሰቦቿ መካከል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናችው የመጀመሪያዋ ሰው ኤሌና ናት። እሷና ባለቤቷ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረጋቸው ትዳራቸውን ታድጎላቸዋል። ሁለት ወንዶች ልጆች አላቸው

ሰርጌ ያቩሽኪን

  • የትውልድ ዘመን፦ 1960 (ሩብትሶቭስክ፣ አልታይ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ለአሥርተ ዓመታት ያህል የብየዳ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። አሁን ቁልፍ ሠሪ ሆኖ እየሠራ ነው። ከወጣትነቱ አንስቶ ጊታር መጫወትና በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ያስደስተዋል

  • በ1990 ባለቤቱን ታቲያናን አገባ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ መጽሐፍ ቢሆንም ለዘመናችን የሚጠቅም ምክር የያዘ መሆኑ ትኩረታቸውን ሳበው። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አላቸው

የክሱ ሂደት

ሐምሌ 22, 2019 ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ ፖሊሶች የወንድም አሌክሳንደር ቦንዳርቹክን እና የወንድም ሰርጌ ያቩሽኪንን መኖሪያ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ፈተሹ። በዚህ ጊዜ ግን ሁለቱም ወንድሞች የታሰሩ ሲሆን ሚስቶቻቸው ለምርመራ ፖሊስ ፊት ቀረቡ። በተጨማሪም ፖሊሶቹ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻቸውን ወሰዱባቸው።

አሌክሳንደር እና ሰርጌ ለሁለት ቀን ያህል ታሰሩ። ከዚያም የኬሜሮቮ ክልል ማዕከላዊ የአውራጃ ፍርድ ቤት ለሁለት ወር ያህል በቁም እስር እንዲቆዩ አደረገ፤ ይህ ብያኔ ስድስት ጊዜ ያህል ተራዝሟል።

ሁለቱም ወንድሞች በቁም እስር ሳሉ ከቤታቸው ከ300 ሜትር ርቀት በላይ መሄድ አይፈቀድላቸውም። በመሆኑም ወደ ሥራ መሄድ አልቻሉም። ሆኖም ሁለቱም ወንድሞች የክስ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት በአካባቢያቸውም ሆነ በአሠሪዎቻቸው ዘንድ ጥሩ ስም አትርፈው ነበር። በመሆኑም አሠሪዎቻቸው መርማሪው ጋ በመደወል ወንድሞች ከ300 ሜትር በላይ እንዳይንቀሳቀሱ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ ጠየቁ። ይሁንና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጓል።

አሌክሳንደር እና ቤተሰቡ በተደጋጋሚ የይሖዋን እጅ ማየት ችለዋል። አሌክሳንደር መሥራት ስለማይችል እንዲሁም የባንክ ሒሳባቸውን እንዳያንቀሳቅሱ ስለታገዱ የገንዘብ ችግር አጋጥሟቸው ነበር። ሆኖም አሌክሳንደር እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ፈተና ከቀድሞው የበለጠ በይሖዋ ላይ መታመን እንዳለብኝ አስተምሮኛል። ከዚህ በፊት ስላላስተዋልኩት ሊሆን ቢችልም አሁን ይሖዋ በእያንዳንዱ ሰዓትና በእያንዳንዱ ቀን ያለማቋረጥ እየረዳኝ እንደሆነ ይሰማኛል። እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ የእሱን ድጋፍና ፍቅር ያላገኘንበት ወቅት የለም።”

የክስ ሂደቱ በወንድም ሰርጌ ላይ ከባድ ውጥረት አስከትሎበት ነበር። በዚህም ምክንያት አንጎሉ ውስጥ የደም መፍሰስ ችግር አጋጥሞታል። የጤና ችግር ቢያጋጥመውም አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ቀጥሏል። እንዲህ ብሏል፦ “የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መቋቋም አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሊሆንብን ቢችልም እነዚህን ችግሮች ቀለል አድርገን መመልከት አለብን።”

ሰርጌ 1 ቆሮንቶስ 15:58 ላይ የሚገኘውን “ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት የምታከናውኑት ሥራ ከንቱ [አይደለም]” የሚለውን ጥቅስ ማስታወሱ ያበረታታዋል። እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ይሖዋ ሁሉንም ነገር ያስታውሳል፤ ያከናወንነውን መልካም ሥራም ፈጽሞ አይረሳም።”

ላለፉት ዓመታት ስደትን በትዕግሥት እየተቋቋሙ ላሉት በሩሲያ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጸለያችንን እንቀጥላለን። “ይሖዋ እሱን በሚፈሩ፣ ታማኝ ፍቅሩን በሚጠባበቁ ሰዎች ይደሰታል” የሚለው ጥቅስ እንደሚያጽናናቸውና እንደሚያበረታታቸው ተስፋ እናደርጋለን።—መዝሙር 147:11