በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም አልቤርት ባትቸዬቭ

ግንቦት 24, 2021
ሩሲያ

ወንድም አልቤርት ባትቸዬቭ በማረፊያ ቤትና በቁም እስር ቢቆይም በአቋሙ እንደጸና ነው

ወንድም አልቤርት ባትቸዬቭ በማረፊያ ቤትና በቁም እስር ቢቆይም በአቋሙ እንደጸና ነው

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ወንድም አልቤርት ባትቸዬቭ ጥፋተኛ ነው ብሎ ፈረደ

ታኅሣሥ 6, 2021 በካረቻየቮ ቺርኬሲያ ሪፑብሊክ የሚገኘው የቺርኬሲያ ከተማ ፍርድ ቤት ወንድም አልቤርት ባትቸዬቭ ጥፋተኛ ነው በማለት የስድስት ዓመት የገደብ እስራት በየነበት። እርግጥ በአሁኑ ወቅት እስር ቤት አይገባም።

አጭር መረጃ

አልቤርት ባትቸዬቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1976 (ካረቻየቭስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ሦስት እህቶችና አንድ ወንድም አለው። እናቱን በሞት ያጣ ሲሆን አረጋዊ አባቱን ይንከባከባል። በወታደራዊ ትምህርት ቤት የጠበቃነት ሙያ ተምሯል፤ በወንጀል ምርመራ ቢሮ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ነበረው

    መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ መሆኑን እርግጠኛ ሆነ። በ2004 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በ2007 ከዣና ጋር ትዳር መሠረተ። በአሁኑ ወቅት በር በመግጠም ሥራ ይተዳደራል። ባለበት የጤና እክል የተነሳ አቅሙ ውስን ነው። እሱና ዣና ተራራ ላይ በመኪና፣ አንዳንዴም በእግር መጓዝ እንዲሁም ከቤት ውጭ ጊዜ ማሳለፍ ይወዳሉ

የክሱ ሂደት

ታኅሣሥ 16, 2019 የፌዴራል ደህንነት አባላት በቺርክየስክ ከተማ የሚገኙ ከአሥር በላይ ቤቶችን በረበሩ። በዚህም ምክንያት ብዙ ወንድሞች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

በማግስቱ ከወንድም አልቤርት ባትቸዬቭ በስተቀር ሁሉም ተለቀቁ። አልቤርት ቢያንስ ለ72 ሰዓታት ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ፤ እንዲሁም ሌሎች እንዲዘምሩና ወደ ይሖዋ እንዲጸልዩ አደራጅቷል በሚል ክስ ተመሠረተበት። አልቤርት የወንጀል ክስ ከተመሠረተበት በኋላ ጓደኞቹና ሌሎች የሚያውቃቸው ሰዎች ፖሊሶች እንደተከታተሏቸው ተናግረዋል።

አልቤርት እንዲህ ብሏል፦ “ማረፊያ ቤት ባስገቡኝ ወቅት ትልቁ የብረት በር ክርችም ብሎ ሲዘጋ ሰውነቴን ውርር አደረገኝ። ከዚያ ቦታ መቼም እንደማልወጣ ተሰማኝ፤ እዚያው የምሞት መስሎኝ ነበር። የባለቤቴና የወንድሞች ሁኔታም በጣም አሳስቦኝ ነበር።”

አልቤርት ለሁለት ወራት ገደማ ማረፊያ ቤት ከቆየ በኋላ እስሩ ወደ ቁም እስር ተቀየረለት። ሆኖም ከአንድ ሳምንት በኋላ በድጋሚ ወደ ማረፊያ ቤት ተወሰደ፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ ለሰባት ሳምንት ቆየ። አልቤርት እንዲህ ብሏል፦ “እስር ቤት ውስጥ በነበርኩበት ወቅት በተለይም ከሌሎች ተገልዬ ብቻዬን በታሰርኩበት ወቅት፣ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበርና በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በቅንዓት መካፈል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይበልጥ ተገነዘብኩ። እንዲህ ዓይነት ልማድ የነበረኝ መሆኑ ብርታት እንዳገኝና እንዳልዳከም በተጨማሪም እምነቴ፣ ጽናቴ፣ ተስፋዬ እንዲሁም ለይሖዋና ለሰዎች ያለኝ ፍቅር እንዳይጠፋ ረድቶኛል።”

እስር ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ከባድ ቢሆንም አልቤርት መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ችሎ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እንድጸና የረዳኝ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ተስፋ እንዳልቆርጥ እንዲሁም የቤተሰቦቼ ናፍቆት ከአቅም በላይ እንዳይሆንብኝ ረድቶኛል።” አልቤርት ከባድ መከራ የደረሰባቸውና ታስረው የነበሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ስሜት ከበፊቱ ይበልጥ እንደገባው ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “እስር ቤት ውስጥ እያለሁ እነዚህ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እውን እና ቅርብ ሆነውልኛል። በጥንት ዘመን የኖሩም ሆኑ በዘመናችን ያሉ ብዙ ወዳጆች እንዳሉኝ ይሰማኛል።”

ሚያዝያ 2020 ፍርድ ቤቱ አልቤርት ለሁለት ወር በቁም እስር እንዲቆይ ወሰነ። ሆኖም ቆይታው አራት ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል። የቁም እስሩ ለአራተኛ ጊዜ የተራዘመው በመጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ ሲሆን እስከ ሰኔ 2021 መጨረሻ አካባቢ ድረስ እንዲቀጥል ተወስኗል።

ይሖዋ ወንድም አልቤርት ባትቸዬቭን ጨምሮ በፈተና ውስጥ ላሉ ታማኝ አገልጋዮቹ በሙሉ ብርታት መስጠቱንና እነሱን መንከባከቡን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—1 ዜና መዋዕል 29:12