በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም አርተር ሎክቪትስኪ ከባለቤቱ ከአና ጋር

ጥር 26, 2021
ሩሲያ

ወንድም አርተር ሎክቪትስኪ የአራት ዓመት እስራት ሊፈረድበት ይችላል

ወንድም አርተር ሎክቪትስኪ የአራት ዓመት እስራት ሊፈረድበት ይችላል

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

ሩሲያ ውስጥ በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት የወንድም አርተር ሎክቪትስኪን ጉዳይ ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት የካቲት 2, 2021 a ቀጠሮ ይዟል። ወንድም አርተር የአራት ዓመት እስራት ሊፈረድበት ይችላል።

አጭር መግለጫ

አርተር ሎክቪትስኪ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1986 (ቤልጎሮድስኮዬ፣ የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ አርተር የሰባት ዓመት ልጅ እያለ አባቱ ሞተበት። አርተር የኤሌክትሪክ ባለሙያ ሲሆን በዋነኝነት የሚሠራው እሳት ከመከላከል ጋር የተያያዘ ሥራ ነው። ትጉህ ሠራተኛ በመሆኑ ተሸልሟል

    አርተር ልጅ እያለ እናቱ ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርበት ረድታዋለች። በ1998 በ11 ዓመቱ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በ2018 ከአና ጋር ተጋቡ። ባልና ሚስቱ ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝና ከቤት ውጭ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች መካፈል ያስደስታቸዋል

የክሱ ሂደት

ግንቦት 2018 ማለትም አርተርና አና በተጋቡ በሦስት ወራቸው ባለሥልጣናቱ የእነዚህን ባልና ሚስት ቤት በረበሩ። ይህ ፍተሻ “የፍርድ ቀን” የሚል የኮድ ስም የተሰጠው ተልእኮ ክፍል ሲሆን 150 የደህንነት አባላት የ22 የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች በርብረዋል። የአርተር እናት የአይሪና ቤትም ከተበረበሩት ቤቶች አንዱ ነው። ሐምሌ 31, 2019 በቢሮቢድዣን ከተማ የሚገኙ የፌዴራል ደህንነት አባላት፣ አርተር በጽንፈኝነት እንቅስቃሴ እንደተካፈለ በመግለጽ የወንጀል ክስ መሠረቱበት። አና እና አይሪናም ለየብቻቸው ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

እነዚህ ክሶች በዚህ ቤተሰብ ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ችግር አስከትለዋል። ባለሥልጣናቱ አርተር የባንክ ሒሳቡን እንዳያንቀሳቅስ አግደውታል። በተጨማሪም አሠሪው ከሥራ እንደሚያሰናብተው ዝቶበታል።

የወንጀል ምርመራው ሂደት የዚህን ቤተሰብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በእጅጉ አውኮታል። አርተር እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። የሳምንቱን (ሌላው ቀርቶ የቀኑን እንኳ) ፕሮግራም ማውጣት አዳጋች ሆኖብናል። [ፖሊሶቹ] ለእነሱ በሚመቻቸው የተለያየ ሰዓት ይጠሩናል። ስለዚህ በየጊዜው ፕሮግራማችን መቀየር ይጠበቅብናል።”

አርተር እና አና የእምነት ባልንጀሮቻቸው ለሚያደርጉላቸው ድጋፍ አመስጋኝ ናቸው። አርተር እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞቻችን በመንፈሳዊም ሆነ በስሜታዊ ሁኔታ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጉልናል። . . . በይሖዋ ሕዝቦች መካከል በመሆናችን እንዲሁም በፍርድ ቤት ለይሖዋ ስም ጥብቅና የመቆም ክብር በማግኘታችን በጣም ደስተኞች ነን! ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ፈጽሞ እንደማይተዋቸው በግልጽ ማየት ይቻላል!”

በተጨማሪም ይህ ቤተሰብ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዞ መቀጠሉ ብርታትና ድፍረት ሰጥቶታል። እርግጥ ነው፣ ይህን ለማድረግ የተቸገሩበት ጊዜ ነበር። “የፍርድ ቀን” ከተባለው ዘመቻ በኋላ ምንም መንፈሳዊ ምግብ እንዳልነበራቸው አርተር ተናግሯል። በመሆኑም መጀመሪያ ላይ ይህ ጉዳይ አሳስቦት ነበር። እሱና ቤተሰቡ መንፈሳዊ ልማዳቸውን ይዘው መቀጠል የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ግራ ገብቶት ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ አንድ መሠረታዊ እውነታ አስታወሰ፤ እንዲህ ብሏል፦ “[የፌዴራል ደህንነት አባላቱ] የጸሎት መብታችንን ሊነጥቁን አይችሉም። ስለዚህ ወዲያውኑ በዚህ ዝግጅት መጠቀም ጀመርን። ለመጽናት የረዳን ጸሎት ነው።”

ይሖዋ ለጸሎታቸው አፋጣኝ ምላሽ የሰጣቸው ሲሆን መንፈሳዊ ልማዳቸውን ይዘው ለመቀጠል የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ አደረገ። አርተር እንዲህ ብሏል፦ “በቋሚነት የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ፣ ለስብሰባዎች ለመዘጋጀትና በቤተሰብ ሆነን መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ጥረት እናደርጋለን። ይህን ማድረጋችን እርስ በርስ ለመቀራረብ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን እጅ ለማየትና አዎንታዊ አመለካከት ይዘን ለመቀጠል ረድቶናል።”

የአምላክን ቃል ከማንበብና ከማጥናት በተጨማሪ ወደፊት በሚመጡት በረከቶች ላይ ማሰላሰላቸውም በጣም ጠቅሟቸዋል። አርተር እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ወደፊቱ ተስፋችን ይበልጥ ማሰብ እንዲሁም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ስንኖር በዓይነ ሕሊናችን ለመሣል ጥረት ማድረግ ጀመርን። ምድርን በማጽዳቱና በግንባታው ሥራ መካፈል እንፈልጋለን። ይህን ማሰባችን ብርታት ሰጥቶናል።”

ይህ ቀን እስኪመጣ ድረስ አርተርና አና በዕብራውያን 13:6 ላይ አዘውትረው ያሰላስላሉ፤ ጥቅሱ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” ይላል። አርተር እንዲህ ብሏል፦ “ባለሥልጣናቱ ነፃነታችንን እና አብረን የመሰብሰብ መብታችንን ሊነፍጉን ይባስ ብሎም እኔና አናን እንዳንገናኝ ሊያግዱን ይችላሉ። ያም ቢሆን ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ይኸውም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና፣ የጸሎት መብታችንን እና የወደፊቱን ተስፋችንን ሊወስዱብን አይችሉም፤ ሁልጊዜ ይህንን ለማስታወስ እንሞክራለን።”

a ቀኑ ሊቀየር ይችላል።