ሚያዝያ 7, 2021
ሩሲያ
ወንድም አናቶሊ ቪሊትኬቪች የፍርድ ቤቱን ብይን በሚጠባበቅበት ወቅት በአቋሙ እንደጸና ነው
ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት የቀረበለትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ
ታኅሣሥ 16, 2021 የባሽኮርቶስታን ሩፑብሊክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንድም አናቶሊ ቪሊትኬቪች ያቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። በመሆኑም መጀመሪያ ላይ የተላለፈበት ፍርድ ይጸናል። እርግጥ በአሁኑ ወቅት እስር ቤት አይገባም።
መስከረም 27, 2021 በኡፋ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም አናቶሊ ጥፋተኛ ነው በማለት በሁለት ዓመት የገደብ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።
አጭር መግለጫ
አናቶሊ ቪሊትኬቪች
የትውልድ ዘመን፦ 1986 (ካባረቭስክ ክልል)
ግለ ታሪክ፦ በአናጺነት ይተዳደራል። በ2008 ከአልዮና ጋር ትዳር መሠረተ። እሱና ባለቤቱ ተራራ መውጣት እንዲሁም ድንኳን ጥለው ማደር ይወዳሉ
ወላጆቹ ከልጅነቱ ጀምሮ ፈጣሪን እንዲወድ ረድተውታል። በተለይ ደግሞ ሰዎችና እንስሳት በሰላም አብረው የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጸው ተስፋ በጣም ያስደስተዋል። በ1997 በ11 ዓመቱ ተጠመቀ
የክሱ ሂደት
ነሐሴ 8, 2018 ወንድም አናቶሊ ቪሊትኬቪች በሩሲያ በአሸባሪነት በተጠረጠሩ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተተ። የሩሲያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሚያዝያ 2017 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ ከጣለ በኋላ ማረፊያ ቤት ከገቡት የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አናቶሊ ቪሊትኬቪች እና ዴኒስ ክሪስተንሰን ይገኙበታል።
መርማሪዎቹ በአናቶሊ እና በአልዮና አፓርትመንት ውስጥ በድብቅ ካሜራ አስቀመጡ። መርማሪዎቹ አናቶሊ ከጓደኞቹ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሲወያይ የቀረጹትን ቪዲዮ መሠረት በማድረግ ወንጀል ፈጽሟል ብለው ከሰሱት። አናቶሊ፣ ጽንፈኛ ተብሎ የተፈረጀ ድርጅትን እንቅስቃሴ በማደራጀት “ወንጀል” ተከስሷል።
አናቶሊ በፖሊሶች በተወሰደበት ወቅት አንደኛው ፖሊስ አልዮናን “ሌላ ባል ፈልጊ” ብሏት ነበር። አናቶሊ በምርመራው ወቅት የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብቼ ነበር። ጥፋተኛ መሆኔን ካላመንኩ ባለቤቴና ለስብሰባ ቤታችን የመጡት ሁሉ ከባድ ቅጣት እንደሚደርስባቸው ፖሊሶቹ ዛቱብኝ። ባለቤቴም እስር ቤት እንደምትገባ በተደጋጋሚ ይነግሩኝ ነበር። እንደነዚህ ባሉት ወቅቶች ይሖዋ የአእምሮ ሰላም እንዲሰጠኝ እጠይቀው ነበር።”
አናቶሊ በማረፊያ ቤት ከሁለት ወር በላይ፣ በቁም እስር ደግሞ ወደ ዘጠኝ ወር ገደማ ያሳለፈ ሲሆን የጉዞ ገደብ ከተጣለበት አንድ ዓመት ተኩል አልፏል። ታስሮ እያለ፣ ስደት የደረሰባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን ስም በማስታወሻ ደብተር ላይ አስፍሮ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እነዚህ ሰዎች ስደት እንዳይደርስባቸው እንዳላደረገ አስታወስኩ፤ ያም ቢሆን ግን ትቷቸዋል ማለት አይደለም። ይህም በጣም ያበረታታኝ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ ለእኔም ተመሳሳይ ነገር እንደሚያደርግልኝ እንድተማመን ረድቶኛል። ከእኔ የሚጠበቀው ታማኝ መሆን ነው።” ባለቤቱ የላከችለት ደብዳቤዎችም ብርታት ሰጥተውታል። እንዲህ ብሏል፦ “አልዮና መጀመሪያ አካባቢ ከላከችልኝ ደብዳቤ በአንዱ ውስጥ ከጓደኞቻችን እና ከቤተሰቦቻችን ጋር የተነሳናቸውን በርካታ ፎቶግራፎችም አካትታ ነበር። በየምሽቱ እነዚህን ፎቶግራፎች እያየሁ ከእነዚያ ሰዎች ጋር ያሳለፍኩትን አስደሳች ጊዜ ለማስታወስ እሞክር ነበር። ይህም አብረውኝ እንደሆኑ እንዲሰማኝ አድርጓል።”
የአናቶሊ እና የአልዮና የታማኝነት ምሳሌ ሁላችንንም ያበረታታናል። በሩሲያ ያሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ከባድ ስደት ቢያጋጥማቸውም በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው እንደቀጠሉ በማየታችን ተደስተናል። ይሖዋ ስለ እነሱ የምናቀርበውን ጸሎት ስለሚሰማን እናመሰግነዋለን።—2 ቆሮንቶስ 1:11