በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም አንቶን ኦስታፔንኮ

ሚያዝያ 28, 2021
ሩሲያ

ወንድም አንቶን ኦስታፔንኮ ማረፊያ ቤት ሳለ መጸለዩና መዘመሩ እንዲጸና ረድቶታል

ወንድም አንቶን ኦስታፔንኮ ማረፊያ ቤት ሳለ መጸለዩና መዘመሩ እንዲጸና ረድቶታል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ወንድም አንቶን ኦስታፔንኮ ጥፋተኛ ነው የሚል ብይን አስተላለፈ

ጥቅምት 25, 2021 የክራስኖያርስ ክልል የሻሪፖቮ ከተማ ፍርድ ቤት የሩሲያ ፍርድ ቤት ወንድም አንቶን ኦስታፔንኮ ጥፋተኛ ነው በማለት የስድስት ዓመት ከሦስት ወር የገደብ እስር በይኖበታል። እርግጥ በአሁኑ ወቅት ወህኒ አይወርድም።

አጭር መግለጫ

አንቶን ኦስታፔንኮ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1991 (ኤኪባስቱዝ፣ ካዛክስታን)

  • ግለ ታሪክ፦ በኃይል ማመንጫ ጣቢያ ውስጥ የውኃ ማፊያ ተቆጣጣሪ ሆኖ ይሠራል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለ እናቱ ለእሱና ለእህቱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ነገረቻቸው። በ2005 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ

    በ2015 ከባለቤቱ ከናታሊያ ጋር ትዳር መሠረተ። እሱና ባለቤቱ የበረዶ ላይ ሸርተቴ መጫወት ያስደስታቸዋል። በተጨማሪም አንቶን ጊታር መጫወት፣ ዓሣ ማጥመድ እንዲሁም ቴኒስ መጫወት ይወዳል

የክሱ ሂደት

ሚያዝያ 19, 2019 የሻሪፖቮ ፖሊሶች የአሥር የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች ከፈተሹ በኋላ፣ ባገኟቸው ወንድሞችና እህቶች ላይ ምርመራ አካሄዱ። ወንድም አንቶን ኦስታፔንኮ ተይዞ ማረፊያ ቤት የገባ ሲሆን ታኅሣሥ 20, 2019 ተለቀቀ። “ጽንፈኛ” ተብሎ የተፈረጀን ድርጅት እንቅስቃሴ በማደራጀት ወንጀል ክስ ተመሠረተበት።

አንቶን ተይዞ በቆየባቸው ስድስት ወራት ውስጥ ሁኔታው በጣም አስጨንቆት ነበር፤ ከዚህም የተነሳ ከደህንነት ካሜራው ዞር ብሎ ክፍሉ ወደሚገኘው የእጅ መታጠቢያ በመሄድ ያለቀሰባቸው ጊዜያት ነበሩ።

በዚህ ጊዜ ዋነኛ የብርታት ምንጭ የሆነለት ጸሎት ነበር። አንቶን “ጽናት ለማዳበር እንዲረዳኝ ይሖዋን እለምነው ነበር” ብሏል። አክሎም እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ብዙ የምማረው ነገር ነበር። በመንፈሳዊ ማደግና ጠንካራ መሆን ችያለሁ። . . . የሚገርመው ነገር፣ [እንዲህ ያለ] ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ የጭንቅላት እውቀት ብቻ የነበረን ነገር ወደ ተግባር መለወጥ የምትችሉበት አጋጣሚ ይከፈትላችኋል። መጽሐፍ ቅዱስ የማታገኙበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ከመታሰሬ በፊት፣ ስለ ይሖዋ የነበረኝ እውቀት ባነበብኩት ነገር ላይ ብቻ የተመሠረተ ነበር። [እስር ቤት ከገባሁ] በኋላ ግን ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ በደንብ አሳይቶኛል። እውነቱን ለመናገር፣ በጣም ደስ ብሎኛል! ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ብቻ ሳይሆን ሁኔታዬን በሚገባ የሚረዳልኝ እንዲሁም በተገቢው ጊዜ ፈጽሞ ባላሰብኩት መንገድ የሚረዳኝና የሚደግፈኝ አፍቃሪ አባት ሆኖልኛል።”

ሌላው ያበረታታው ነገር የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመሩ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ሁሌም መዝሙሮችን አብረን እንዘምር ነበር፤ ይህም መዝሙሮቹን በቃላችን እንድንይዛቸው ረድቶናል። ማረፊያ ቤት በገባሁበት ጊዜ ይህ በጣም ጠቅሞኛል። መብራቶቹ ከጠፉ በኋላ መጸለይና መዘመር ያስደስተኝ ነበር፤ ይህም ልቤ ተረጋግቶ ጥሩ እንቅልፍ እንድተኛ ረድቶኛል።”

በአሁኑ ጊዜ አንቶን የፍርድ ውሳኔውን እየተጠባበቀ ሲሆን ሥራውን መሥራቱን ቀጥሏል። ሆኖም የሻሪፖቮ ከተማን ለቆ መውጣት አይፈቀድለትም። ይህ ገደብ፣ እናቱን ወደ ሆስፒታል ቀጠሮዎቿ ይዟት መሄድ እንዳይችል አድርጎታል።

ይሖዋ ስደትን በጽናት ተቋቁመው ላሉ ወንድሞቻችን ሰላም እንደሚሰጣቸው በመተማመን ወደ እሱ መጸለያችንን እንቀጥላለን።—ዮሐንስ 14:27