ሚያዝያ 5, 2021
ሩሲያ
ወንድም አንድሬ ጉቢን በእምነቱ ምክንያት ክስ ቢመሠረትበትም በአቋሙ ጸንቷል
ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ፍርድ ቤት ወንድም አንድሬ ጉቢን ጥፋተኛ ነው የሚለውን ብይን ቀለበሰ
የካቲት 1, 2022 የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል ፍርድ ቤት ወንድም አንድሬ ጉቢን ጥፋተኛ ነው የሚለውን ብይን ቀለበሰ። ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይ ወደ በታች ፍርድ ቤቱ ተመልሷል።
መስከረም 9, 2021 በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል የሚገኘው የቢሮቢድዣን አውራጃ ፍርድ ቤት ወንድም አንድሬ ጉቢን ጥፋተኛ ነው በማለት የሁለት ዓመት ከስድስት ወር የገደብ እስራት በየነበት። እርግጥ አንድሬ አሁን ወህኒ አይወርድም።
አጭር መግለጫ
አንድሬ ጉቢን
የትውልድ ዘመን፦ 1974 (ሳራን ሲቲ፣ ካዛክስታን)
ግለ ታሪክ፦ ታላቅ ወንድም እና እህት አለው። በልጅነቱ ቤተሰቡን ለመደገፍ ሲል ከትምህርት ሰዓት በኋላ የቁልፍ ሠሪ ረዳት ሆኖ ይሠራ ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ የቅርጽ ማውጫ ማሽን እና ከባድ ማሽኖች ላይ ሠርቷል። በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል፣ ግጥም መጻፍ እንዲሁም የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ይወዳል
በዓለም ላይ የሚታየው ግፍና ክፋት ከልጅነቱ ጀምሮ ይረብሸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና ውስጣዊ ሰላም ያገኘ ከመሆኑም ሌላ የሕይወትን ዓላማ አወቀ። በምድር ላይ ፍትሕና ሰላም እንደሚሰፍን የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ራሱን ለይሖዋ አምላክ እንዲወስን አነሳሳው። በ1991 በ17 ዓመቱ ተጠመቀ። በ2007 ከታትያና ጋር ትዳር መሠረተ። በ2011 ወደ ቢሮቢድዣን ተዛወረ
የክሱ ሂደት
የካቲት 12, 2020 የፌዴራል ደህንነት አገልግሎት አባላት በወንድም አንድሬ ጉቢን ላይ ምርመራ ማካሄድ ጀመሩ። መስከረም 17, 2020 ክሱ በፍርድ ቤት መታየት ጀመረ።
በአንድሬ ላይ የተመሠረተው ክስ በአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል በሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከተመሠረቱት 19 ክሶች አንዱ ነው። በወንድሞቻችን ላይ ክስ የተመሠረተባቸው “የፍርድ ቀን” የሚል የኮድ ስም የተሰጠው የፍተሻ ዘመቻ ከተካሄደ በኋላ ነው። ግንቦት 17, 2018 በቢሮቢድዣን የሚገኙ 150 ሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት የ22 የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች በርብረዋል። ባለሥልጣናቱ የወንድሞቻችንን የባንክ ካርዶች፣ ገንዘብ፣ ፎቶግራፎች፣ ኮምፒውተሮችና የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ወርሰዋል።
ባለሥልጣናቱ አንድሬና ታትያና የባንክ ሒሳባቸውን እንዳያንቀሳቅሱ አግደዋቸዋል። በዚህም ምክንያት ባልና ሚስቱ ለከባድ የኢኮኖሚ ችግር ተዳርገዋል። ለወራት የዘለቀው የፍርድ ሂደት በታትያና ጤንነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ያም ቢሆን ባልና ሚስቱ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው ማንበባቸው በጣም አጽናንቷቸዋል። በተለይም አስቸጋሪ ሁኔታን መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር በእጅጉ ረድቷቸዋል።
አንድሬ ከመንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶች ያገኘው ድጋፍ በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለውን እምነት አጠናክሮለታል። ለምሳሌ አንድ ቀን አንድሬ በጣም ተጨንቆ ነበር። በመሆኑም እንደ እሱ የወንጀል ክስ ለተመሠረተበት አንድ ወንድም ስሜቱን አውጥቶ ነገረው። ያ ወንድም በመጀመሪያ የአንድሬ ስሜት እንደገባው አረጋገጠለት። ከዚያም ወንድም፣ ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ስም መሰደድን እንደ መብት አድርጎ እንደቆጠረው ለአንድሬ አስታወሰው። አንድሬ እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ሲለኝ ተረጋጋሁ። የአባታችንን ፈቃድ መፈጸሜን ለመቀጠል ቆርጫለሁ።”
አንድሬና ታትያና ከአምላክ ቃል እንዲሁም ከመንፈሳዊ ቤተሰባችን መጽናኛና ብርታት ማግኘታቸውን እንዲቀጥሉ እንጸልያለን። “እውነተኛውን አምላክ የሚፈሩ ሰዎች . . . የኋላ ኋላ መልካም እንደሚሆንላቸው” እርግጠኞች ነን።—መክብብ 8:12